ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 9:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ሰማይ ጠቀስ ቅጥር ያላቸው ታላላቅ ከተሞች ያሏቸውን፣ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ አስለቅቀህ ለመግባት ዮርዳኖስን አሁን ትሻገራለህ።

2. ዔናቃውያን ብርቱና ቁመተ ረጃጅም ሕዝቦች ናቸው፤ ስለ እነርሱ ታውቃለህ፤ “ዔናቃውያንን ማን ሊቋቋማቸው ይችላል?” ሲባልም ሰምተሃል።

3. ይሁን እንጂ እንደሚባላ እሳት ከፊትህ ቀድሞ የሚሻገረው አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሆኑን ዛሬ እርግጠኛ ሁን፤ እነርሱን ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ድል ያደርጋቸዋል፤ አንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ታስወጣቸዋለህ፤ በፍጥነትም ትደመስሳቸዋለህ።

4. አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነርሱን ከፊትህ ካስወጣቸው በኋላ፣ “ይህችን ምድር እንድወርስ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደዚህ ያመጣኝ፣ ከጽድቄ የተነሣ ነው” ብለህ በልብህ አታስብ። በዚህ አይደለም፤ እነዚህን አሕዛብ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከፊትህ የሚያሳድዳቸው በክፋታቸው ምክንያት ነው።

5. ምድራቸውን ገብተህ የምትወርሳት ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሣ ሳይሆን፣ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚህን አሕዛብ ከክፋታቸው የተነሣ ከፊትህ ስለሚያባርራቸው ነው።

6. ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህችን መልካም ምድር እንድትወርሳት የሚሰጥህ ከጽድቅህ የተነሣ አለመሆኑን አስተውል፤ አንተ ዐንገተ ደንዳና ነህና።

7. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቈጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብፅ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፅህ ነህ።

8. በኮሬብ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለቊጣ አነሣሣችሁት፤ እርሱም እናንተን ሊያጠፋችሁ እጅግ ተቈጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 9