ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 29:3-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እነዚያን ከባድ ፈተናዎች፣ ታምራዊ ምልክቶችና ታላላቅ ድንቆች በገዛ ዐይኖቻችሁ አይታችኋል።

4. ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያይ ዐይን ወይም የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም።

5. በምድረ በዳ በመራኋችሁ በእነዚያ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም።

6. ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) እንደሆንሁ ታውቁ ዘንድ ነው።

7. ወደዚህ ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፣ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው።

8. ምድራቸውንም ወስደን፤ ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን።

9. እንግዲህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወ ንላችሁ፣ የዚህን ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ።

10. እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፣ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም ሌሎች የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ቆማችኋል፤

11. ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ እንጨትህን እየፈለጡ፣ ውሃህንም እየቀዱ በሰፈርህ የሚኖሩ መጻተኞችም አብረውህ ቆመዋል።

12. እዚህ የቆምኸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ ከአንተ ጋር ወደሚያደርገውና በመሓላ ወደሚያጸናው ኪዳን ከአምላክህከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ጋር ትገባ ዘንድ፣

13. ለአንተ በሰጠው ተስፋና ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላክህ (ኤሎሂም) ይሆን ዘንድ፣ አንተም ሕዝቡ መሆንህን፣ በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 29