ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 23:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ብልቱ የተቀጠቀጠ ወይም የተቈረጠ ማናቸውም ሰው ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።

2. ዲቃላም ይሁን የዲቃላው ዘር የሆነ ሁሉ፣ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እንኳን ቢሆን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።

3. አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወይም ማናቸውም የእርሱ ዘር፣ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ ቢሆን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።

4. ምክንያቱም ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በጒዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እህል ውሃ ይዘው አልተቀበሏችሁም፤ በመስጴጦምያ በምትገኘው በፐቶር ይኖር የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምም አንተን እንዲረግም በገንዘብ ገዙት።

5. ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በለዓምን አልሰማውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስለሚወድህ ርግማኑን በረከት አደረገልህ።

6. በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ሰላምን ለእነርሱ አትመኝ።

7. ወንድምህ ስለ ሆነ ኤዶማዊውን አትጸየፈው፤ መጻተኛ ሆነህ በአገሩ ኖረሃልና ግብፃዊውን አትጥላው።

8. ለእነርሱ የተወለዱላቸው የሦስተኛው ትውልድ ልጆች ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ መግባት ይችላሉ።

9. ጠላትህን ለመውጋት ወጥተህ በሰፈርህ ጊዜ፤ ከማናቸውም ርኵሰት ራስህን ጠብቅ።

10. ከመካከላችሁ ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር ከሰፈር ወጥቶ እዚያው ይቈይ።

11. እየመሸ ሲመጣ ግን ገላውን ይታጠብ፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ወደ ሰፈሩ ይመለስ።

12. ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ።

13. ከትጥቅህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቈፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት።

14. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን።

15. አንድ ባሪያ ከአሳዳሪው ኰብልሎ ወደ አንተ ቢመጣ፣ ለአሳዳሪው አሳልፈህ አትስጠው።

16. ደስ በሚያሰኘው ቦታና ራሱ በመረጠው ከተማ በመካከልህ ይኑር፤ አንተም አታስጨንቀው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 23