ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከእግዚአብሔር ጉባኤ መለየት

1. ብልቱ የተቀጠቀጠ ወይም የተቈረጠ ማናቸውም ሰው ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።

2. ዲቃላም ይሁን የዲቃላው ዘር የሆነ ሁሉ፣ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እንኳን ቢሆን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።

3. አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወይም ማናቸውም የእርሱ ዘር፣ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ ቢሆን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።

4. ምክንያቱም ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በጒዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እህል ውሃ ይዘው አልተቀበሏችሁም፤ በመስጴጦምያ በምትገኘው በፐቶር ይኖር የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምም አንተን እንዲረግም በገንዘብ ገዙት።

5. ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በለዓምን አልሰማውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስለሚወድህ ርግማኑን በረከት አደረገልህ።

6. በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ሰላምን ለእነርሱ አትመኝ።

7. ወንድምህ ስለ ሆነ ኤዶማዊውን አትጸየፈው፤ መጻተኛ ሆነህ በአገሩ ኖረሃልና ግብፃዊውን አትጥላው።

8. ለእነርሱ የተወለዱላቸው የሦስተኛው ትውልድ ልጆች ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ መግባት ይችላሉ።

የጦር ሰፈር ንጽሕና አጠባበቅ

9. ጠላትህን ለመውጋት ወጥተህ በሰፈርህ ጊዜ፤ ከማናቸውም ርኵሰት ራስህን ጠብቅ።

10. ከመካከላችሁ ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር ከሰፈር ወጥቶ እዚያው ይቈይ።

11. እየመሸ ሲመጣ ግን ገላውን ይታጠብ፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ወደ ሰፈሩ ይመለስ።

12. ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ።

13. ከትጥቅህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቈፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት።

14. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን።

ልዩ ልዩ ሕጎች

15. አንድ ባሪያ ከአሳዳሪው ኰብልሎ ወደ አንተ ቢመጣ፣ ለአሳዳሪው አሳልፈህ አትስጠው።

16. ደስ በሚያሰኘው ቦታና ራሱ በመረጠው ከተማ በመካከልህ ይኑር፤ አንተም አታስጨንቀው።

17. ወንድ ወይም ሴት እስራኤላዊ የቤተ ጣዖት አመንዝራ አይሁን።

18. ለዝሙት አዳሪ ሴት ወይም ለወንደቃ የተከፈለውን ዋጋ ለማናቸውም ስእለት አድርገህ ለመስጠት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቤት አታምጣ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሁለቱንም ይጸየፋቸዋልና።

19. የገንዘብ፣ የእህል ወይም የማንኛውንም ነገር ወለድ ለማግኘት ለወንድምህ በወለድ አታበድር።

20. ባዕድ ለሆነ ሰው ወለድ ማበደር ትችላለህ፤ ነገር ግን ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እጅህ በሚነካው በማናቸውም ነገር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲባርክህ ለእስራኤላዊ ወንድምህ በወለድ አታበድረው።

21. ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስእለት ከተሳልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አጥብቆ ከአንተ ይሻዋልና፣ ኀጢአት እንዳይሆንብህ ለመክፈል አትዘግይ።

22. ሳትሳል ብትቀር ግን በደለኛ አትሆንም።

23. በአንደበትህ የተናገርኸውን ሁሉ ለመፈጸም ጠንቃቃ ሁን፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በገዛ አንደበትህ ፈቅደህ ስእለት ተስለሃልና።

24. ወደ ባልንጀራህ የወይን ተክል ቦታ በምትገባበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል መብላት ትችላለህ፤ ነገር ግን አንዳችም በዕቃህ አትያዝ።

25. ወደ ባልንጀራህ ዕርሻ በምትገባበት ጊዜ፣ እሸት መቅጠፍ ትችላለህ፤ በሰብሉ ላይ ግን ማጭድ አታሳርፍበት።