ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 22:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. የወንድምህን አህያ ወይም ልብስ ወይም የጠፋበትን ማናቸውንም ነገር ስታገኝ እንደዚሁ አድርግ፤ በቸልታ አትለፈው።

4. የወንድምህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታየው፣ በእግሩ እንዲቆምለት ርዳው እንጂ ዐልፈኸው አትሂድ።

5. ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፤ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ እንዲህ የሚያደርገውን ሁሉ አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይጸየፈዋልና።

6. በመንገድ ስታልፍ፣ አንዲት ወፍ ጫጩቶቿን ወይም ዕንቁላሎቿን የታቀፈችበትን ጐጆ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ ብታገኝ፣ እናቲቱን ከነጫጩቶቿ አትውሰድ፤

7. ጫጩቶቿን መውሰድ ትችላለህ፤ እናቲቱን ግን መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህም እንዲረዝም ልቀቃት፤

8. አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ፣ ከጣራው ላይ ሰው ወድቆ በቤትህ ላይ የደም በደል እንዳታመጣ፣ በጣራው ዙሪያ መከታ አብጅለት።

9. በወይን ተክል ቦታህ ውስጥ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤ ይህን ካደረግህ፣ የዘራኸው ሰብል ብቻ ሳይሆን፣ የወይን ፍሬህም ይጠፋል።

10. በሬና አህያ በአንድ ላይ ጠምደህ አትረስ።

11. ሱፍና በፍታ አንድ ላይ ተፈትሎ የተሠራ ልብስ አትልበስ።

12. በምትለብሰው ልብስ ላይ በአራቱ ማእዘኖች ዘርፍ አድርግ።

13. አንድ ወንድ ሚስት አግብቶ አብሮአት ከተኛ በኋላ ቢጠላት፣

14. ስሟንም በማጥፋት፣ “ይህችን ሴት አገባኋት፤ ዳሩ ግን በደረስሁባት ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁም” ቢል፣

15. የልጂቱ አባትና እናት ድንግልናዋን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው በከተማዪቱ በር ወዳሉት አለቆች ይምጡ።

16. የልጂቱም አባት ለአለቆቹ እንዲህ ይበል፤ “ልጄን ለዚህ ሰው ዳርሁለት፤ እርሱ ግን ጠላት፤

17. ስሟንም በማጥፋት፣ ‘ልጅህን ከነድንግልናዋ አላገኘኋትም’ ብሎኛል፤ ነገር ግን የልጄ ድንግልና ማረጋገጫ ይኸውላችሁ፤” ከዚያም ወላጆቿ የደሙን ሸማ በከተማዪቱ አለቆች ፊት ይዘርጉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 22