ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 22:20-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ሆኖም ክሱ እውነት ሆኖ ሴቲቱ ድንግል ለመሆኗ ምንም ማረጋገጫ ማቅረብ ካልተቻለ፣

21. ገና በአባቷ ቤት ሳለች በማመንዘር በእስራኤል ውስጥ ወራዳ ተግባር ፈጽማለችና ወደ አባቷ ቤት ደጃፍ ያምጧት፤ እዚያም የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሯት። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

22. አንድ ሰው፣ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፣ አብሮአት የተኛው ሰውና ሴቲቱ ሁለቱም ይገደሉ፤ ክፉውን ከእስራኤል ማስወገድ አለብህ።

23. አንድ ሰው የታጨች ድንግል በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርሷ ጋር ቢተኛ፣

24. ልጃገረዲቱ በከተማ ውስጥ እያለች አስጥሉኝ ብላ ስላልጮኸች፣ ሰውየውም የሌላን ሰው ሚስት አስገድዶ ስለደፈረ፣ ሁለቱንም ወደ ከተማ ደጃፍ ወስዳችሁ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሯቸው። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

25. ነገር ግን አንድ ሰው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማ ውጭ አግኝቶ በማስገደድ ቢደፍራት፣ ይህን ድርጊት የፈጸመው ሰው፣ ብቻ ይገደል።

26. በልጃገረዲቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉባት፤ ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት ምንም አልሠራችም፤ ይህ ዐይነቱ ጒዳይ፣ አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ከሚገድል ሰው አድራጎት ጋር የሚመሳሰል ነው።

27. ምክንያቱም ሰውየው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማ ውጭ ስላገኛትና ብትጮኽም እንኳ ለርዳታ የደረሰላት ማንም ሰው ስላልነበር ነው።

28. አንድ ሰው ያልታጨች ልጃገረድ አግኝቶ በማስገደድ ቢደርስባትና ቢጋለጡ፣

29. ሰውየው ለልጅቷ አባት አምሳ ስቅል ብር ይክፈል፤ ልጃገረዲቱን አስገድዶ ደፍሮአታልና እርሷን ማግባት አለበት፤ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊፈታት አይችልም።

30. አንድ ሰው የአባቱን ሚስት ማግባት የለበትም፤ የአባቱንም መኝታ አያርክስ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 22