ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 22:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ሲባዝን ብታየው፣ ወደ እርሱ መልሰህ አምጣለት እንጂ ዝም ብለህ አትለፈው፤

2. ወንድምህ በአቅራቢያህ ባይኖር፣ ወይም የማን መሆኑን የማታውቅ ከሆነ፣ ባለቤቱ ፈልጎት እስኪመጣ ድረስ፣ ወደ ቤትህ ወስደህ ከአንተ ዘንድ አቈየው፤ ከዚያም መልሰህ ስጠው።

3. የወንድምህን አህያ ወይም ልብስ ወይም የጠፋበትን ማናቸውንም ነገር ስታገኝ እንደዚሁ አድርግ፤ በቸልታ አትለፈው።

4. የወንድምህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታየው፣ በእግሩ እንዲቆምለት ርዳው እንጂ ዐልፈኸው አትሂድ።

5. ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፤ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ እንዲህ የሚያደርገውን ሁሉ አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይጸየፈዋልና።

6. በመንገድ ስታልፍ፣ አንዲት ወፍ ጫጩቶቿን ወይም ዕንቁላሎቿን የታቀፈችበትን ጐጆ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ ብታገኝ፣ እናቲቱን ከነጫጩቶቿ አትውሰድ፤

7. ጫጩቶቿን መውሰድ ትችላለህ፤ እናቲቱን ግን መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህም እንዲረዝም ልቀቃት፤

8. አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ፣ ከጣራው ላይ ሰው ወድቆ በቤትህ ላይ የደም በደል እንዳታመጣ፣ በጣራው ዙሪያ መከታ አብጅለት።

9. በወይን ተክል ቦታህ ውስጥ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤ ይህን ካደረግህ፣ የዘራኸው ሰብል ብቻ ሳይሆን፣ የወይን ፍሬህም ይጠፋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 22