ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 21:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፣ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፣ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች።

14. በእርሷ ደስተኛ ባትሆን፣ ወደምትፈልገው አንድትሄድ ነጻነት ስጣት፤ ውርደት ላይ ጥለሃታልና ልትሸጣት ወይም እንደ ባሪያ ልትቈጥራት አይገባህም።

15. አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፤ አንደኛዋን የሚወዳት፣ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፣ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት በኵር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፣

16. ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፣ የብኵርናን መብት ከማይወዳት ሚስቱ ከወለደው በኵር ልጅ ገፎ፣ ከሚወዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ፣ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤

17. ይልቁንም ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሀብት ሁሉ ሁለት እጅ ድርሻውን በመስጠት ብኵርናውን ያስታውቅ፤ ያ ልጅ የአባቱ ኀይል መጀመሪያ ነውና፤ የብኵርና መብት የራሱ ነው።

18. አንድ ሰው፣ የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፣ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣

19. አባትና እናቱ ይዘው በሚኖሩበት ከተማ በር ወዳሉት አለቆች ያምጡት፤

20. “ይህ ልጃችን እልከኛና ዐመፀኛ ነው፤ አይታዘዘንም፤ አባካኝና ሰካራም ነው” ብለው ለአለቆች ይንገሯቸው።

21. ከዚያም በኋላ የከተማዪቱ ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ ክፉውንም ከመካከልህ አስወግድ፤ እስራኤልም ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል።

22. አንድ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ፈጽሞ ቢገደልና በድኑ በዕንጨት ላይ ቢሰቀል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 21