ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 2:2-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤

3. “በዚህ በኰረብታማ አገር ዙሪያ እስኪበቃችሁ ተንከራታችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን ተመለሱ።

4. ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ።

5. ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታህል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሷቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ።

6. ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።”

7. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኮአችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጒዞ ጠብቆአችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።

8. ስለዚህ በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮች የሆኑ ወንድሞቻችንን ዐልፈናቸው ሄድን። ከኤላትና ከጽዮንጋብር ከሚመጣው ከዓረባ መንገድ ተመልሰን፣ በሞአብ ምድረ በዳ መንገድ ተጓዝን።

9. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ከሞዓባውያን ምድር አንዳችም መሬት ስለማልሰጣችሁ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሷቸው፤ ዔርን ለሎጥ ዘሮች ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ” አለኝ።

10. በዚያም ጠንካራና ቊጥራቸው የበዛ እንዲሁም እንደ ዔናቃውያን ረጃጅም የሆኑ ኤሚማውያን ይኖሩ ነበር።

11. እነዚህም እንደ ዔናቃውያን ሁሉ ራፋይማውያን ናቸው ተብለው ይገመቱ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚማውያን ብለው ይጠሯቸዋል።

12. ሖራውያን ቀድሞ በሴይር ይኖሩ ነበር፤ የዔሳው ዘሮች ግን ከዚያ አሳደው አስወጧቸው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ርስት አድርጎ በሰጠው ምድር ላይ እስራኤል እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህም ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።

13. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) “አሁኑኑ ተነሡና የዘሬድን ደረቅ ወንዝ ተሻገሩ” አለን፤ እኛም ወንዙን ተሻገርን።

14. ቃዴስ በርኔን ከለቀቅንበት ጊዜ አንሥቶ የዘሬድን ደረቅ ወንዝ እስከ ተሻገርንበት ጊዜ ድረስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ዐለፈ። በዚያን ጊዜም ለጦርነት ብቁ የሆኑት የዚያ ትውልድ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ አስቀድሞ በማለው መሠረት ከሰፈሩ ፈጽመው ዐለቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 2