ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 17:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. በአንድ የነፍስ ግድያ ዐይነትና በሌላ፣ በአንድ ዐይነት ሕጋዊ ክርክርና በሌላ፣ ወይም በአንድ የክስ ዐይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጒዳይ ቢነሣ፣ ከዐቅምህ በላይ የሆነ ጒዳይ በከተሞችህ ውስጥ ቢያጋጥምህ፣ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ፤

9. ካህናት ወደሆኑት ሌዋውያንና በዚያን ጊዜ ዳኛ ወደ ሆነው ሰው ሄደህ፣ ስለ ጒዳዩ ጠይቃቸው፤ እነርሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል።

10. አንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡህ ውሳኔ መሠረት ፈጽም፤ እንድ ትፈጽም የሚሰጡህን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርግ።

11. በሚያስተምሩህ ሕግና በሚሰጡህ መመሪያዎች መሠረት ፈጽም። እነርሱ ከሚነግሩህ ቀኝም ግራም አትበል።

12. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ለማገልገል በዚያ የሚቆመውን ካህን ወይም ዳኛ የሚንቅ ይገደል፤ ከእስራኤልም መካከል ክፉውን አስወግድ።

13. ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲሰማ ይፈራል፤ ከዚያ ወዲያም እንዲህ ያለውን የንቀት ድርጊት አይደግመውም።

14. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፣ በምትወርሳትና በምትቀመጥባት ምድር፣ “በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ፣ እኔም በላዬ ንጉሥ ላንግሥ” ብትል፣

15. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚመርጠውን ንጉሥ በላይህ ታነግሣለህ፤ ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንጂ፣ እስራኤላዊ ወንድምህ ያልሆነውን ባዕድ በላይህ አታንግሥ።

16. ንጉሡም ብዙ ፈረሶችን ለራሱ አያብዛ፤ ወይም ደግሞ የፈረሰኞችን ቊጥር ለመጨመር ሕዝቡን ወደ ግብፅ አይመልስ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “በዚያ መንገድ ፈጽሞ አትመለሱ” ብሎአችኋልና።

17. ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ፤ ብዙ ብርና ወርቅም አያግበስብስ።

18. በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ የዚህን ሕግ ቅጅ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ በጥቅልል መጽሐፍ ለራሱ ይጻፍ።

19. አምላኩን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ማክበር ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉና ይህን ሥርዐት በጥንቃቄ ይከተል ዘንድ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ያንብበው፤

20. እርሱና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ረጅም ዘመን ይገዙ ዘንድ፣ ከሕጉ ቀኝም ግራም አይበል፤ ራሱን ከሌሎች ወንድሞቹ በላይ የተሻለ አድርጎ አይቊጠር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 17