ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 17:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንከን ወይም ጒድለት ያለበትን በሬ ወይም በግ በእርሱ ዘንድ አስጸያፊ ነውና ለአምላክህለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አትሠዋ።

2. እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ አብሮህ የሚኖር ወንድ ወይም ሴት ኪዳኑን በማፍረስ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ክፉ ድርጊት ሲፈጽም ቢገኝ፣

3. ትእዛዜንም በመተላለፍ ባዕዳን አማልክትን ያመለከ፣ ለእርሱም ማለትም ለፀሓይ ወይም ለጨረቃ ወይም ለሰማይ ከዋክብት የሰገደ፣

4. አንተም ይህ መደረጉን ብትሰማ፣ ነገሩን በጥንቃቄ መርምር፤ የተባለውም እውነት ከሆነና እንዲህ ያለው አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ዘንድ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣

5. ይህን ክፉ ድርጊት የፈጸመውን ወንድ ወይም ሴት ወደ ከተማ ደጅ ወስደህ፣ ያን ሰው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።

6. ሞት የሚገባው ሰው፣ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት ይገደል፤ ነገር ግን በአንድ ሰው ምስክርነት ብቻ ማንም ሰው አይገደል።

7. ሲገደልም መጀመሪያ የምስክሮቹ እጅ፣ ቀጥሎም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይረፍበት፤ ክፉን ከመካከልህ አስወግድ።

8. በአንድ የነፍስ ግድያ ዐይነትና በሌላ፣ በአንድ ዐይነት ሕጋዊ ክርክርና በሌላ፣ ወይም በአንድ የክስ ዐይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጒዳይ ቢነሣ፣ ከዐቅምህ በላይ የሆነ ጒዳይ በከተሞችህ ውስጥ ቢያጋጥምህ፣ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ፤

9. ካህናት ወደሆኑት ሌዋውያንና በዚያን ጊዜ ዳኛ ወደ ሆነው ሰው ሄደህ፣ ስለ ጒዳዩ ጠይቃቸው፤ እነርሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል።

10. አንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡህ ውሳኔ መሠረት ፈጽም፤ እንድ ትፈጽም የሚሰጡህን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርግ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 17