ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 15:13-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በምታሰናብተውም ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው።

14. ከመንጋህ፣ ከዐውድማህና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን ስጠው።

15. አንተም ራስህ በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን ትእዛዝ ዛሬ የምሰጥህም በዚሁ ምክንያት ነው።

16. ነገር ግን አገልጋይህ፣ አንተንና ቤተ ሰብህን ከመውደዱና ከአንተም ጋር ደስተኛ ሆኖ ከመኖሩ የተነሣ፣ “ከአንተ መለየት አልፈልግም” ቢልህ፣

17. ጆሮውን ከቤትህ መዝጊያ ላይ በማስደገፍ በወስፌ ትበሳዋለህ፤ ከዚያም ዕድሜ ልኩን አገልጋይህ ይሆናል። በሴት አገልጋይህም ላይ እንደዚሁ አድርግ።

18. አገልጋይህን ዐርነት ማውጣቱ ከባድ መስሎ አይታይህ፤ የስድስት ዓመት አገልግሎቱ፣ አንድ የቅጥር ሠራተኛ የሚሰጠው አገልግሎት ዕጥፍ ነውና። አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በምታደርገው ነገር ሁሉ ይባርክሃል።

19. የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎችህን ተባዕት በኵር ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቀድስ። የበሬህን በኵር አትሥራበት፤ የበግህንም በኵር አትሸልት፤

20. እርሱ በሚመርጠው ስፍራ አንተና ቤተ ሰብህ በየዓመቱ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበሉታላችሁ።

21. አንድ እንስሳ እንከን ካለበት፣ አንካሳ ወይም ዕውር፣ ወይም ደግሞ ማናቸውም ዐይነት ከባድ ጒድለት ያለበት ከሆነ፣ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አትሠዋው፤

22. በየከተሞችህም ትበላዋለህ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነውም ሆነ ያልሆነው ሰው፣ እንደ ድኵላ እንደ ዋላ ይበላዋል።

23. ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 15