ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 15:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት አድርግ።

2. አፈጻጸሙም እንደሚከተለው ነው፤ እያንዳንዱ አበዳሪ ለእስራኤላዊ ባልንጀራው ያበደረውን ይተውለት፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የዕዳ ምሕረት አውጆአልና፣ አበዳሪው፣ እስራኤላዊ ባልንጀራውን ወይም ወንድሙን ዕዳውን እንዲከፍለው አይጠይቀው።

3. ለባዕድ ያበደርኸውን መጠየቅ ትችላለህ፤ ወንድምህ ከአንተ የተበደረውን ማናቸውንም ዕዳ ግን ተወው።

4. ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፣ በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤

5. ይህ የሚሆነውም ለአምላክህለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፈጽመህ ስትታዘዝና ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ስትከተል ብቻ ነው።

6. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ስለሚባርክህ፣ አንተ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ እንጂ ማንም አንተን አይገዛህም።

7. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ካሉት ከተሞች ባንዲቱ ውስጥ ድኻ ቢኖር፣ በድኻ ወንድምህ ላይ ልብህን አታጨክንበት፤ ወይም እጅህን ወደ ኋላ አትሰብስብበት።

8. ይልቁንስ እጅህን ፍታለት፤ የሚያስፈልገውንም ሁሉ ቅር ሳይልህ አበድረው።

9. “ዕዳ የሚሠረዝበት ሰባተኛው ዓመት ተቃርቦአል” የሚል ክፉ ሐሳብ አድሮብህ፣ በችግረኛ ወንድምህ ላይ እንዳትጨክንና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር፣ እርሱም በአንተ ላይ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኾ በደለኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!

10. በልግስና ስጠው፤ ስትሰጠውም ልብህ አይጸጸት፤ ከዚህም የተነሣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሥራህ ሁሉና እጅህ ባረፈበት በማናቸውም ነገር ይባርክሃል።

11. በምድሪቱ ላይ ድኾች ምንጊዜም አይጠፉም፤ ስለዚህ በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞችህ፣ ለድኾችና ለችግረኞች እጅህን እንድትዘረጋ አዝሃለሁ።

12. ወገንህ የሆነ ዕብራዊ ወንድን ወይም ሴትን ገዝተህ ስድስት ዓመት ካገለገለህ፣ በሰባተኛው ዓመት ዐርነት አውጣው።

13. በምታሰናብተውም ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 15