ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 14:16-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ጒጒት፣ ጋጋኖ፣ የውሃ ዶሮ፣

17. ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣ እርኩም፣

18. ሽመላ፣ ማናቸውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጅላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ ናቸው።

19. ክንፍ ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው፤ እነርሱን አትብሏቸው።

20. ንጹሕ የሆነውን ማናቸውንም ክንፍ ያለውን ፍጡር ግን ብሉ።

21. አንተ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ነህና የሞተውን ሁሉ አትብላ፤ ከከተሞችህ በአንዲቱ ለሚኖር መጻተኛ ስጠው፤ ይብላውም፤ ለውጭ አገር ሰው ሽጠው። የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል።

22. በየዓመቱ ከእርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ።

23. ምንጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ብላ።

24. ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባርኮህ ሳለ፣ መንገዱ ቢርቅብህና እግዚአብሔር (ያህዌ) የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ ዐሥራትህን ወደዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልህ፣

25. ዐሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ።

26. በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ ማለትም የቀንድ ከብት፣ በግ፣ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተ ሰብህ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት በዚያ ትበላላችሁ፤ ሐሤትም ታደርጋላችሁ።

27. የራሱ ድርሻ ወይም ርስት ስለሌለው በከተሞችህ የሚኖረውን ሌዋዊ ቸል አትበለው።

28. በየሦስት ዓመቱ መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል ዐሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች።

29. ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፣ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፣ አንተንም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 14