ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ንጹሕና ንጹሕ ያልሆነ ምግብ

1. እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ልጆች ናችሁ፤ ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትቦጭቁ፤ ከግንባራችሁ በላይ ያለውን ጠጒር አትላጩ፤

2. ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንድትሆንለት እግዚአብሔር (ያህዌ) በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ አንተን መርጦሃል።

3. ማናቸውንም ርኩስ ነገር አትብላ።

4. የምትበሏቸው እንስሳት እነዚህ ናቸው፤ በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣

5. ዋላ፣ ድኵላ፣ ሰስ፣ የበረሓ ፍየል፣ ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ አጋዘን።

6. ሰኰናው ስንጥቅ የሆነውን፣ ለሁለት የተከፈለውንና የሚያመሰኳ ማናቸውንም እንስሳ ብላ።

7. ነገር ግን ከሚያመሰኩት ወይም ሰኰናቸው ከተሰነጠቀ እንስሳት መካከል ግመልን፣ ጥንቸልንና ሽኮኮን አትብሉ፤ እነርሱ ቢያመሰኩ እንኳ፣ ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ባለመሆኑ፣ በሥርዐቱ መሠረት በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው።

8. ዐሳማም እንደዚሁ ርኩስ ነው፤ ምንም እንኳ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም፣ ስለማያመሰኳ፣ እርሱ ለእናንተ ንጹሕ አይደለም፤ የእነዚህን ሥጋ አትብሉ፤ ጥምባቸውንም አትንኩ።

9. በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ፍጡራን ሁሉ ክንፍና ግልፋፊ ያለውን ማናቸውንም ብሉ፤

10. ክንፍና ግልፋፊ የሌለውን ግን አትብሉ፤ ለእናንተ ርኩስ ነው።

11. ንጹሕ የሆነውን ወፍ ሁሉ መብላት ትችላላችሁ።

12. የሚከተሉትን ግን አትበሉም፤ እነርሱም፦ ንስር፣ ገዴ፣ ዓሣ አውጪ፣

13. ጭልፊት፣ ጭላት፣ ማናቸውም ዐይነት አድኖ በል አሞራ፣

14. ማናቸውም ዐይነት ቁራ፣

15. ሰጎን፣ ጠላቋ፣ ዝዪ፣ ማናቸውም ዐይነት በቋል፣

16. ጒጒት፣ ጋጋኖ፣ የውሃ ዶሮ፣

17. ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣ እርኩም፣

18. ሽመላ፣ ማናቸውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጅላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ ናቸው።

19. ክንፍ ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው፤ እነርሱን አትብሏቸው።

20. ንጹሕ የሆነውን ማናቸውንም ክንፍ ያለውን ፍጡር ግን ብሉ።

21. አንተ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ነህና የሞተውን ሁሉ አትብላ፤ ከከተሞችህ በአንዲቱ ለሚኖር መጻተኛ ስጠው፤ ይብላውም፤ ለውጭ አገር ሰው ሽጠው። የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል።

ዐሥራት

22. በየዓመቱ ከእርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ።

23. ምንጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ብላ።

24. ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባርኮህ ሳለ፣ መንገዱ ቢርቅብህና እግዚአብሔር (ያህዌ) የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ ዐሥራትህን ወደዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልህ፣

25. ዐሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ።

26. በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ ማለትም የቀንድ ከብት፣ በግ፣ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተ ሰብህ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት በዚያ ትበላላችሁ፤ ሐሤትም ታደርጋላችሁ።

27. የራሱ ድርሻ ወይም ርስት ስለሌለው በከተሞችህ የሚኖረውን ሌዋዊ ቸል አትበለው።

28. በየሦስት ዓመቱ መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል ዐሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች።

29. ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፣ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፣ አንተንም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው።