ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 11:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. እነዚህን ቃሎቼን፣ በልባችሁና በአእምሮአችሁ አኑሯቸው፤ በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፣ በግምባራችሁም ላይ ይሁኑ።

19. ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ ቤት ስትቀመጥ፣ መንገድ ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣ ስለ እነዚሁ አጫውታቸው።

20. በቤትህ መቃኖችና በግቢህ በሮች ላይ ጻፋቸው፤

21. ይህን ካደረጋችሁ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር የእናንተና የልጆቻችሁ ዘመን ከምድር በላይ ያሉ ሰማያትን ርቀት ያህል ይሆናል።

22. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትወዱ ዘንድ፣ በመንገዶቹም ሁሉ ትሄዱና ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ እንድትከተሏቸው የምሰጣችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣

23. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል፤ እናንተም፣ ከእናንተ ይልቅ ታላላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ታስለቅቃላችሁ።

24. በእግራችሁ የምትረግጡት ስፍራ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው ባሕር ይደርሳል።

25. ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ማስደንገጣችሁንና መፈራታችሁን በምትሄዱበት በየትኛውም ምድር ሁሉ ላይ ያሳድራል።

26. እነሆ፤ ዛሬ በረከትንና መርገምን በፊታችሁ አኖራለሁ፤

27. በረከቱ ዛሬ የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ስትፈጽሙ ሲሆን፣

28. መርገሙ ደግሞ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች የማትፈጽሙ፣ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ለመከተል እኔ ከማዛችሁ መንገድ የምትወጡ ከሆነ ነው።

29. ልትወርሳት ወደ ምትሄድባት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚያስገባህ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፣ መርገሙን ደግሞ በጌባል ተራራ ላይ ታሰማለህ።

30. እነዚህ ተራሮች የሚገኙት ከዮርዳኖስ ማዶ ፀሓይ በምትጠልቅበት አቅጣጫ ካለው መንገድ በስተ ምዕራብ በዓረባ በሚኖሩ የከነዓናውያን ምድር ውስጥ ከጌልገላ ፊት ለፊት፣ በሞሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ አይደለምን?

31. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጣችሁ ምድር ትገቡባትና ትወርሷት ዘንድ ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ስለ ሆነ፣ ምድሪቱን ወርሳችሁ በምትኖሩባት ጊዜ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 11