ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 10:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. በዚያን ጊዜ፣ ዛሬም እንደሚያደርገው ያገለግል ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት እንዲቆምና በስሙ እንዲባርክ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) የኪዳኑን ታቦት እንዲሸከም እግዚአብሔር (ያህዌ) የሌዊን ነገድ ለየ።

9. ሌዋዊ በወንድሞቹ መካከል ድርሻም ሆነ ርስት የሌለው ከዚህ የተነሣ ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገረው መሠረት ርስቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።

10. እኔም በመጀመሪያው ጊዜ እንዳደረግሁት፣ በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ በዚህ ጊዜም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ገና ሰማኝ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተን ሊያጠፋ አልፈቀደም።

11. ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ሂድ፤ ለአባቶቻቸው ለመስጠት ወደማልሁላቸው ምድር ገብተው እንዲወርሱ ሕዝቡን ምራ” አለኝ።

12. አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣

13. መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?

14. ሰማያት፣ ሰማየ ሰማያት፣ ምድርና በእርሷም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነው።

15. ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) አባቶችህን ስላፈቀረ፣ ወደዳቸው፤ ዛሬም እንደሆነው የእነርሱ ዘር የሆናችሁትን እናንተን ከአሕዛብ ሁሉ ለይቶ መረጣችሁ።

16. ስለዚህ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙት፤ ከእንግዲህም ወዲያ ዐንገተ ደንዳና አትሁኑ።

17. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የአማልክት አምላክ (ኤሎሂም)፣ የጌቶች ጌታ (አዶናይ) ታላቅ አምላክ (ኤሎሂም)፣ ኀያልና የሚያስፈራ፣ አድልዎ የማያደርግ፣ መማለጃም የማይቀበል ነውና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 10