ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 10:12-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣

13. መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?

14. ሰማያት፣ ሰማየ ሰማያት፣ ምድርና በእርሷም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነው።

15. ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) አባቶችህን ስላፈቀረ፣ ወደዳቸው፤ ዛሬም እንደሆነው የእነርሱ ዘር የሆናችሁትን እናንተን ከአሕዛብ ሁሉ ለይቶ መረጣችሁ።

16. ስለዚህ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙት፤ ከእንግዲህም ወዲያ ዐንገተ ደንዳና አትሁኑ።

17. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የአማልክት አምላክ (ኤሎሂም)፣ የጌቶች ጌታ (አዶናይ) ታላቅ አምላክ (ኤሎሂም)፣ ኀያልና የሚያስፈራ፣ አድልዎ የማያደርግ፣ መማለጃም የማይቀበል ነውና።

18. እርሱ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች ይፈርዳል፤ መጻተኛውንም ምግብና ልብስ በመስጠት ይወዳል።

19. ስለዚህ እናንተም በግብፅ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኛን ውደዱ።

20. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፍራ፤ አምልከውም፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቅ፤ በስሙም ማል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 10