ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 1:15-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ስለዚህ እኔም የየነገዶቻችሁን አለቆች ጥበበኞችንና የተከበሩትን ሰዎች ተቀብዬ፣ ሻለቆች፣ መቶ አለቆች፣ አምሳ አለቆችና ዐሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዱ ሹማምት በማድረግ በእናንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሾምኋቸው።

16. በዚያን ጊዜም ዳኞቻችሁን እንዲህ ስል አዘዝኋቸው፤ “በወንድሞቻችሁ መካከል የሚነሣውን ክርክር ያለ አድልዎ እዩት፤ ሙግቱ ወንድማማች በሆኑ እስራኤላውያን መካከል ወይም በአንድ እስራኤላዊና በመጻተኛ መካከል ቢሆን፣ በትክክል ፍረዱ።

17. በፍርድ አድልዎ አታድርጉ፤ ትልቁንም ትንሹንም እኩል እዩ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ማንኛውንም ሰው አትፍሩ። ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ሁሉ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔ አየዋለሁ።”

18. በዚያን ጊዜ ማድረግ የነበረባችሁን ሁሉ ነገርኋችሁ።

19. ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን።

20. እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤

21. እነሆ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ምድሪቱን ሰጥቶአችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።”

22. ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ።

23. ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ።

24. እነርሱም ተነሥተው ወደ ኰረብታማው አገር ከወጡ በኋላ ወደ ኤሽኮል ሸለቆ መጥተው ምድሪቱን ሰለሉ።

25. ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን።

26. እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ።

27. በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጒረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብፅ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን፣ በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 1