ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 6:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት ሌላውን ማስተስረያ እንዲሆንለት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው፤ በሬሳ አጠገብ በመገኘቱ ኀጢአት ሠርቶአልና። በዚያኑ ዕለት ጠጒሩን ይቀድስ።

12. ራሱን የተለየ ያደረገበትን ጊዜ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መቀደስ አለበት፤ እንዲሁም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ። ያለፉት ቀኖች አይቈጠሩም፤ በተለየበት ጊዜ ረክሶአልና።

13. “ ‘እንግዲህ ናዝራዊ የመለየቱ ጊዜ ሲያበቃ ሥርዐቱ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ እንዲመጣ ይደረጋል።

14. እዚያም መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ፤ ይኸውም፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኀጢአት መሥዋዕት እንዲሁም እንከን የሌለበት አውራ በግ ለኅብረት መሥዋዕት ሲሆን፣

15. ከእነዚህም ጋር የሚቀርበውን የእህልና የመጠጥ ቍርባን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ማለት ከላመ ዱቄት በዘይት የተለወሱ ዕንጎቻዎች እንዲሁም በስሱ የተጋገረና ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ያምጣ።

16. “ ‘ካህኑ እነዚህን የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቀርባል።

17. በመሶብ ያለውን እርሾ የሌለበት ቂጣ እንዲሁም አውራ በጉን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉና ከመጠጡ ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ።

18. “ ‘ከዚያም ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጒር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጨው፤ ጠጒሩንም ወስዶ ከኅብረቱ መሥዋዕት ሥር በሚነደው እሳት ውስጥ ይጨምረው።

19. “ ‘ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጒር ከተላጨ በኋላ፣ ካህኑ የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች እንዲሁም ከመሶቡ ላይ እርሾ የሌለበትን አንድ ወፍራምና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ ናዝራዊው ያስይዘው

20. ከዚያም ካህኑ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም የተቀደሱ ናቸው። ከተወዘወዘው ፍርምባና ከቀረበው ወርች ጋር የተቀደሱ የካህኑ ድርሻ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል።

21. “ ‘ስእለቱን ለመፈጸም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለሚሳል ናዝራዊ ሕጉ ይኸው ነው፤ ሊቀርብ ከሚችለው በላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለመስጠት ቃል ለሚገባው ነገር እንደ ናዝራዊነቱ በተሳለው መሠረት መሆን አለበት። በናዝራዊነት ሕግ መሠረት የተሳለውን ስእለት መፈጸም ይገባዋል።’ ”

22. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን አለው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 6