ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 35:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. “ከሚወርሱት ርስት ላይ ለሌዋውያን የሚኖሩባቸውን ከተሞች እንዲሰጧቸው እስራኤላውያንን እዘዛቸው፤ በየከተሞቹ ዙሪያም የግጦሽ መሬት ሰጧቸው።

3. ከተሞቹ ለእነርሱ መኖርያ፣ የግጦሽ መሬቱ ለከብቶቻቸው፣ ለበግና ለፍየል መንጎቻቸውና ለሌሎቹም እንስሶቻቸው ይሆናሉ።

4. “በየከተሞቹ ዙሪያ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸውም የግጦሽ መሬት ከከተማው ቅጥር አንድ ሺህ ክንድ ይዘረጋል።

5. ከዚያም ከተማውን መካከል በማድረግ ወደ ምሥራቅ ሁለት ሺህ ክንድ፣ ወደ ደቡብ ሁለት ሺህ ክንድ፣ ወደ ምዕራብ ሁለት ሺህ ክንድ፣ ወደ ሰሜን ሁለት ሺህ ክንድ ከከተማው ውጭ ለካ፤ እነዚህንም ቦታዎች ለከተሞቹ የግጦሽ መሬት ያደርጓቸዋል።

6. “ለሌዋውያኑ ከምትሰጧቸው ከተሞች ስድስቱ፣ ሰው የገደለ ሸሽቶ የሚጠጋባቸው መማጸኛ ከተሞች ይሆናሉ፤ በተጨማሪም አርባ ሁለት ከተሞች ስጧቸው፤

7. የግጦሽ መሬቶቻቸውን ጨምሮ በጠቅላላው አርባ ስምንት ከተሞች ለሌዋውያኑ ስጧቸው።

8. እስራኤላውያን ከወረሷት ምድር ላይ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ከተሞች እያንዳንዱ ነገድ እንዳለው ድርሻ መጠን ይሆናል። ብዙ ካለው ነገድ ላይ ብዙ ከተሞች እንዲሁም ጥቂት ካለው ነገድ ላይ ጥቂት ከተሞችን ውሰዱ።”

9. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

10. “እስራኤላውያንን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ጊዜ፣

11. ሳያስበው ሰው የገደለ ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች እንዲሆኑ መማጸኛ ከተሞችን ምረጡ።

12. እነዚህም፣ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ዘንድ ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ የሚሸሽባቸው የመማጸኛ ከተሞች ይሆናሉ።

13. እነዚህ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ስድስት ከተሞች መማጸኛ ከተሞቻችሁ ይሆናሉ።

14. ስለዚህ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስቱን እንዲሁም በከነዓን ሦስቱን የመማጸኛ ከተሞች አድርጋችሁ ስጡ።

15. እነዚህም ስድስት ከተሞች ሳያስበው ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው እንዲሸሽባቸው ለእስራኤላውያን፣ ለመጻተኞችና በመካከላቸው ለሚኖር ለማንኛውም ሕዝብ የመማጸኛ ቦታዎች ይሆናሉ።

16. “ ‘አንድ ሰው ሌላውን እንዲሞት በብረት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 35