ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 3:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. “የሌዊን ነገድ አምጥተህ ካህኑን አሮንን በአገልግሎቱ እንዲረዱት ከፊቱ አቁማቸው፤

7. በመገናኛው ድንኳን የማደሪያውን አገልግሎት በመፈጸም ለእርሱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ የሚያስፈልጉትን ተግባሮች ያከናውኑ፤

8. የማደሪያውን ሥራ በመሥራትና የእስራኤላውያንን ግዴታ በመወጣት የመገናኛውን ድንኳን ሁሉ ይጠብቁ።

9. ሌዋውያኑን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ተለይተው ለእርሱ ፈጽመው የተሰጡ ናቸው።

10. አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ እነርሱም ክህነታቸውን ይጠብቁ፤ ሌላ ሰው ማደሪያውን ቢቀርብ ግን ይገደል።”

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

12. “እነሆ፤ በኵር ሆኖ በሚወለደው ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ወስጃለሁ፤ ስለዚህ ሌዋውያን የእኔ ናቸው፤

13. በኵር የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና። በግብፅ ምድር በኵር የሆነውን ሁሉ በመታሁ ዕለት ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ማናቸውንም የእስራኤልን በኵር ለራሴ ለይቻለሁ፤ የእኔ ይሁን። እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።”

14. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ምድረ በዳ፣

15. “ሌዋውያንን በየቤታቸውና በየጐሣቸው ቍጠር፤ የምትቈጥረውም አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ ነው” አለው።

16. ስለዚህ ሙሴ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል በታዘዘው መሠረት እነዚህን ቈጠራቸው።

17. የሌዊ ልጆች ስምጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ነው።

18. የጌድሶን ልጆች ጐሣ ስምሎቢኒና ሰሜኢ ነው።

19. የቀዓት ጐሣዎች፤እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮን፣ ዑዝኤል።

20. የሜራሪ ጐሣዎች፤ሞሖሊና ሙሲ።እንግዲህ የሌዋውያን ጐሣዎች በየቤተ ሰባቸው ሲቈጠሩ እነዚህ ናቸው።

21. የሎቤናና የሰሜአ ጐሣዎች ከጌርሶን ወገን ናቸው፤ እነዚህ የጌርሶን ጐሣዎች ነበሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 3