ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 3:41-51 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

41. በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ከብቶች ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን ከብቶች ለእኔ አድርጋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።”

42. ስለዚህ ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤላውያንን በኵር ሁሉ ቈጠረ፤

43. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው በየስማቸው የተመዘገቡት ወንድ በኵሮች ሁሉ ብዛታቸው ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር።

44. ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

45. “በእስራኤላውያን በኵሮች ምትክ ሌዋውያኑን፣ በከብቶቻቸውም ምትክ የሌዋውያኑን ከብቶች ውሰድ፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

46. ቍጥራቸው ከሌዋውያን ቍጥር በሁለት መቶ ሰባ ሦስት በልጦ የተገኘውን እስራኤላውያን በኵሮች ለመዋጀት፣

47. ለእያንዳንዱ በኵር ክብደቱ ባለ ሃያ አቦሊ በሆነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ልክ አምስት አምስት ሰቅል ተቀበል፤

48. የተረፉትንም እስራኤላውያን ለመዋጀት ገንዘቡን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።”

49. ስለዚህ ሙሴ በሌዋውያኑ ተዋጅተው ቍጥራቸው ትርፍ ከሆነው በኵሮች ላይ የመዋጃውን ገንዘብ ተቀበለ፤

50. ከእስራኤላውያን በኵሮች ላይ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ሰቅል ሰበሰበ።

51. ሙሴም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል በታዘዘው መሠረት የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጣቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 3