ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 3:32-45 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. ዋናው የሌዋውያን አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነው፤ እርሱም መቅደሱን ለመጠበቅ ኀላፊ በሆኑት ላይ ተሹሞ ነበር።

33. የሞሖላውያንና የሙሳያውያን ጐሣዎች ከሜራሪ ወገን ናቸው፤ እነዚህም የሜራሪ ጐሣዎች ነበሩ።

34. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች ሁሉ ብዛታቸው ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበር።

35. የሜራሪም ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ይሆናል፤ የሜራሪም ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።

36. ሜራሪያውያንም የማደሪያውን ድንኳን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎች፣ ምሰሶዎቹ የሚቆሙባቸውን እግሮች፣ የማደሪያ ዕቃዎችን ሁሉና ከነዚሁ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ለመጠበቅ ተሹመው ነበር።

37. እንዲሁም የአደባባዩን ዙሪያ ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ከነካስማቸውና ከነገመዶቻቸው ይጠብቃሉ።

38. ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹ ከማደሪያው ድንኳን በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይሰፍራሉ፤ እነርሱም እስራኤላውያንን ወክለው ማደሪያ ድንኳኑን ለመጠበቅ ኀላፊዎች ይሆናሉ፤ ወደ ማደሪያው ድንኳን የሚቀርብ ማንኛውም ሌላ ሰው ግን ይገደል።

39. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው፣ ሙሴና አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በየጐሣቸው የቈጠሩአቸው የሌዋውያን ወንዶች ልጆች ጠቅላላ ብዛት ሃያ ሁለት ሺህ ነበር።

40. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኵር ሆነው የተወለዱትን፣ አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን እስራኤላውያን ወንዶች ሁሉ ቍጠር፤ ዝርዝራቸውንም ያዝ።

41. በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ከብቶች ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን ከብቶች ለእኔ አድርጋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።”

42. ስለዚህ ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤላውያንን በኵር ሁሉ ቈጠረ፤

43. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው በየስማቸው የተመዘገቡት ወንድ በኵሮች ሁሉ ብዛታቸው ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር።

44. ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

45. “በእስራኤላውያን በኵሮች ምትክ ሌዋውያኑን፣ በከብቶቻቸውም ምትክ የሌዋውያኑን ከብቶች ውሰድ፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 3