ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 20:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሙሴና አሮን ከማኅበረ ሰቡ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው በግንባራቸው ተደፉ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ተገለጠላቸው።

7. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

8. “በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብሰቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል። አንተም ለማኅበረ ሰቡ ከዐለቱ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እነርሱና ከብቶቻቸውም ይጠጣሉ።”

9. ስለዚህም ሙሴ ልክ እንደታዘዘው በትሩን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወሰደ።

10. እርሱና አሮንም ማኅበሩን በዐለቱ ፊት አንድ ላይ ሰበሰቡ፤ ሙሴም፣ “እናንት ዐመፀኞች አድምጡ፤ ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” አላቸው።

11. ከዚያም ሙሴ እጁን ዘርግቶ በበትሩ ዐለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ውሃውም ተንዶለዶለ፤ ማኅበረ ሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ።

12. ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን፣ “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረሰብ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” አላቸው።

13. እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር የተጣሉበት፣ እርሱም ቅዱስ መሆኑን በመካከላቸው የገለጠበት ይህ የመሪባ ውሃ ነበር።

14. ሙሴ ከቃዴስ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤“ወንድምህ እስራኤል የሚለው ይህ ነው፤ የደረሰብን መከራ ሁሉ ምን እንደሆነ አንተም ታውቃለህ።

15. የቀድሞ አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፤ እኛም እዚያ ብዙ ዘመን ኖርን። ግብፃውያን እኛንም አባቶቻችንንም አሠቃዩን፤

16. ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) በጮኽን ጊዜ ግን ጩኸታችንን ሰማ፤ መልአክ ልኮም ከግብፅ አወጣን።“አሁንም ያለነው እዚሁ ቃዴስ በግዛትህ ድንበር ላይ ባለችው ከተማ ነው።

17. ስለዚህ በአገርህ እንድናልፍ እባክህን ፍቀድልን፤ በየትኛውም ዕርሻ ወይም የወይን ተክል ውስጥ አንገባም፤ ከየትኛውም ጒድጓድ ውሃ አንጠጣም። የንጉሡን አውራ ጐዳና ይዘን ከመጓዝ በስተቀር፣ ግዛትህን አልፈን እስክንሄድ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።”

18. ኤዶም ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤“በዚህ በኩል አታልፉም፤ እናልፋለን የምትሉ ከሆነ በሰልፍ ወጥተን በሰይፍ እንመታችኋለን።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 20