ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 19:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ከዚህ በኋላ ካህኑ ልብሱን በውሃ ማጠብ፣ ሰውነቱንም መታጠብ አለበት፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ሊመለስ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።

8. የሚያቃጥለውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ፣ ሰውነቱንም በውሃ መታጠብ አለበት፤ እርሱም ደግሞ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።

9. “ንጹሕ የሆነ ሰው የጊደሯን ዐመድ አፍሶ ከሰፈሩ ውጭ በመውሰድ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ያኑረው፤ ይህም ለመንጻቱ ውሃ እንዲውል በእስራኤል ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ይሆናል፤ ከኀጢአትም ለመንጻት ይጠቅማል።

10. የጊደሯን ዐመድ የሚያፈሰውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ አለበት፤ ያም ሰው እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤላውያን እንዲሁም በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች የሚሆን ዘላለማዊ ሥርዐት ነው።

11. “የሞተን ሰው በድን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል።

12. በሦስተኛውና በሰባተኛውም ቀን ሁለመናውን በውሃው ያንጻ፤ ንጹሕም ይሆናል። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ካላነጻ ግን ንጹሕ አይሆንም።

13. የሞተን ሰው በድን ነክቶ ራሱን ያላነጻ ማንኛውም ሰው የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማደሪያ ያረክሳል፤ ያም ሰው ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። የሚያነጻው ውሃ ስላልተረጨበት ርኩስ ነው፤ ከርኵሰቱም አልተላቀቀም።

14. “አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ የሚፈጸመው ሥርዐት የሚከተለው ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ በዚያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል፤

15. እንዲሁም ያልተከደነ ማንኛውም ክፍት ዕቃ የረከሰ ይሆናል።

16. “ሜዳ ላይ በሰይፍ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ወይም ደግሞ ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል።

17. “ለረከሰውም ሰው፣ ለማንጻት ከተቃጠለው የጊደር ዐመድ ላይ ማሰሮ ውስጥ በማድረግ በላዩ የምንጭ ውሃ ይጨምሩበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 19