ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 18:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “ለእኔ በሚቀርበው መባ ላይ ኀላፊነትን የሰጠሁህ እኔው ራሴ ነኝ፤ እስራኤላውያን የሚያቀርቡልኝም የተቀደሰ መባ ሁሉ ለአንተና ለልጆችህ መደበኛ ድርሻችሁ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ።

9. ለእኔ ከሚቀርብልኝ እጅግ ከተቀደሰው መባ ሁሉ፣ በእሳት የማይቃጠለው የራስህ ድርሻ ይሆናል፤ እጅግ የተቀደሰ አድርገው ከሚያመጡልኝ ስጦታ ከእህል ቊርባንም ሆነ ከኀጢአት ወይም ከበደል መሥዋዕት የሚነሣው ሁሉ የአንተና የልጆችህ ድርሻ ነው።

10. እጅግ ቅዱስ መሆኑን በማሰብ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ እያንዳንዱም ወንድ ከዚሁ ይብላ፤ ይህ ለአንተም የተቀደሰ ነው።

11. “እስራኤላውያን ከሚያቀርቡት ስጦታ፣ ከሚወዘወዘው ቊርባን ተለይቶ የሚቀመጠው ስጦታ ሁሉ የአንተ ይሁን። ይህንም ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት የነጻ ማንኛውም ሰው ከዚሁ መብላት ይችላል።

12. “እስራኤላውያን የመከር በኵራት አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጡትን ምርጥ የወይራ ዘይት በሙሉ፣ ምርጥ የሆነውን አዲስ የወይን ጠጅና እህል ሁሉ ለእናንተ ሰጥቻችኋለሁ።

13. ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያመጡት የምድሪቱ በኵር ፍሬ ሁሉ የአንተ ይሆናል። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይህን መብላት ይችላል።

14. “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ የተሰጠ በእስራኤል ያለ ማንኛውም ነገር ሁሉ የአንተ ነው።

15. ማሕፀን የሚከፍትና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ሰውም ሆነ እንሰሳ የአንተ ነው፤ ነገር ግን ማንኛውም በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅና ንጹሕ ካልሆነ እንስሳ በኵር ሆኖ የተወለደውን ተባዕት ሁሉ ዋጀው።

16. እነዚህም አንድ ወር ሲሆናቸው ሃያ ጌራ በሚመዝነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ፣ በተወሰነው በመዋጃው ዋጋ በአምስት ሰቅል ጥሬ ብር ትዋጀዋለህ።

17. “የተቀደሱ ስለሆኑ የበሬ፣ የበግ ወይም የፍየል በኵር የሆኑትን አትዋጃቸውም፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፤ ሥባቸውንም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ ታቃጥለዋለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 18