ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 18:3-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እነርሱም በአንተ ኀላፊነት ሥር ሆነው የድንኳኑን አገልግሎት በሙሉ ያከናውኑ፤ ይሁን እንጂ ወደ መቅደሱ ዕቃዎችም ሆነ ወደ መሠዊያው አይጠጉ፤ ከተጠጉ ግን እነርሱም አንተም ትሞታላችሁ።

4. እነርሱም የመገናኛውን ድንኳን ለመንከባከብ ማለትም በድንኳኑ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ኀላፊነት በመውሰድ አብረዋችሁ ይሁኑ፤ ከዚህ በተረፈ ግን እናንተ ወዳላችሁበት ማንም ሰው አይጠጋ።

5. “በእስራኤላውያን ላይ ዳግም ቊጣ እንዳይደርስባቸው የመቅደሱና የመሠዊያው እንክብካቤ ኀላፊነት የሚመለከተው እናንተን ይሆናል።

6. ከእስራኤላውያን መካከል ወገኖቻችሁን ሌዋውያንን ለእናንተ ስጦታ አድርጌ እኔ ራሴ መርጫቸዋለሁ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ ሁሉ እንዲሠሩ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጡ ናቸው።

7. ይሁን እንጂ በመሠዊያው ላይ የሚደረገውንና በመጋረጃ ውስጥ ያለውን ማንኛውንም የክህነት አገልግሎት የምትፈጽሙት አንተና ልጆችህ ብቻ ናችሁ፤ የክህነቱን አገልግሎት ስጦታ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ። ከእናንተ በስተቀር ወደ መቅደሱ የሚጠጋ ቢኖር ግን ይገደል።”

8. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “ለእኔ በሚቀርበው መባ ላይ ኀላፊነትን የሰጠሁህ እኔው ራሴ ነኝ፤ እስራኤላውያን የሚያቀርቡልኝም የተቀደሰ መባ ሁሉ ለአንተና ለልጆችህ መደበኛ ድርሻችሁ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ።

9. ለእኔ ከሚቀርብልኝ እጅግ ከተቀደሰው መባ ሁሉ፣ በእሳት የማይቃጠለው የራስህ ድርሻ ይሆናል፤ እጅግ የተቀደሰ አድርገው ከሚያመጡልኝ ስጦታ ከእህል ቊርባንም ሆነ ከኀጢአት ወይም ከበደል መሥዋዕት የሚነሣው ሁሉ የአንተና የልጆችህ ድርሻ ነው።

10. እጅግ ቅዱስ መሆኑን በማሰብ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ እያንዳንዱም ወንድ ከዚሁ ይብላ፤ ይህ ለአንተም የተቀደሰ ነው።

11. “እስራኤላውያን ከሚያቀርቡት ስጦታ፣ ከሚወዘወዘው ቊርባን ተለይቶ የሚቀመጠው ስጦታ ሁሉ የአንተ ይሁን። ይህንም ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት የነጻ ማንኛውም ሰው ከዚሁ መብላት ይችላል።

12. “እስራኤላውያን የመከር በኵራት አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጡትን ምርጥ የወይራ ዘይት በሙሉ፣ ምርጥ የሆነውን አዲስ የወይን ጠጅና እህል ሁሉ ለእናንተ ሰጥቻችኋለሁ።

13. ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያመጡት የምድሪቱ በኵር ፍሬ ሁሉ የአንተ ይሆናል። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይህን መብላት ይችላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 18