ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 18:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. “የተቀደሱ ስለሆኑ የበሬ፣ የበግ ወይም የፍየል በኵር የሆኑትን አትዋጃቸውም፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፤ ሥባቸውንም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ ታቃጥለዋለህ።

18. የሚወዘወዘው ቊርባን ፍርምባና የቀኙ ወርች የአንተ እንደሆነ ሁሉ የእነዚህም ሥጋ የአንተ ይሆናል።

19. እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚያቀርቡት ከተቀደሰ ቊርባን የሚለየው ሁሉ ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለአንተና ለዘሮችህ ዘላለማዊ የጨው ኪዳን ነው።”

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “ከምድራቸው የምትካፈለው ርስት፣ ከእነርሱም የምታገኘው ድርሻ የለህም፤ በእስራኤላውያን መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።

21. “በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግሉበት ጊዜ ለሚሠሩት ሥራ ደመወዝ እንዲሆናቸው ከእስራኤል የሚወጣውን ዐሥራት ሁሉ ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ።

22. አድራጎቱ ኀጢአት ስለ ሆነ ሞት እንዳ ያስከትልባቸው ከእንግዲህ ወዲያ እስራኤላውያን ወደ መገናኛው ድንኳን አይጠጉ።

23. በመገናኛው ድንኳን የሚከናወነውን ሥራ የሚሠሩት ሌዋውያን ናቸው፤ በዚያም ለሚፈጸመው በደል ኀላፊነቱን ይሸከማሉ። ይህም ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው፤ ሌዋውያን በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይሰጣቸውም።

24. በዚህ ፈንታም እስራኤላውያን መባ አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡትን ዐሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም እነርሱን በተመለከተ፣ ‘በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይኖራቸውም’ ያልኩት በዚሁ ምክንያት ነው።”

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

26. “ሌዋውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ርስት አድርጌ የምሰጣችሁን ዐሥራት ከእስራኤላውያን በምትቀበሉበት ጊዜ፣ እናንተም ካገኛችሁት ላይ አንድ ዐሥርኛ በማውጣት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አድጋችሁ ታቀርባላችሁ።

27. ቊርባናችሁም ከዐውድማ እንደ ገባ እህል ወይም ከመጭመቂያ እንደ ወጣ ወይን ሆኖ ይቈጠርላችኋል።

28. እናንተም ከእስራኤላውያን ላይ ከምትቀበሉት ዐሥራት ሁሉ በዚሁ ዐይነት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ ታቀርባላችሁ፤ ከዚሁም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የሆነውን ዐሥራት ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ።

29. ከምትቀበሉት ሁሉ ምርጥና እጅግ የተቀደሰውን ክፍል የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ አድርጋችሁ ታቀር ባላችሁ።

30. “ሌዋውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ምርጥ የሆነውን ክፍል በምታቀርቡበት ጊዜ፣ እንደ ዐውድማ ምርት ወይም እንደ ወይን መጭመቂያ ውጤት ሆኖ ይቈጠርላችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 18