ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 18:11-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “እስራኤላውያን ከሚያቀርቡት ስጦታ፣ ከሚወዘወዘው ቊርባን ተለይቶ የሚቀመጠው ስጦታ ሁሉ የአንተ ይሁን። ይህንም ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት የነጻ ማንኛውም ሰው ከዚሁ መብላት ይችላል።

12. “እስራኤላውያን የመከር በኵራት አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጡትን ምርጥ የወይራ ዘይት በሙሉ፣ ምርጥ የሆነውን አዲስ የወይን ጠጅና እህል ሁሉ ለእናንተ ሰጥቻችኋለሁ።

13. ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያመጡት የምድሪቱ በኵር ፍሬ ሁሉ የአንተ ይሆናል። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይህን መብላት ይችላል።

14. “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ የተሰጠ በእስራኤል ያለ ማንኛውም ነገር ሁሉ የአንተ ነው።

15. ማሕፀን የሚከፍትና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ሰውም ሆነ እንሰሳ የአንተ ነው፤ ነገር ግን ማንኛውም በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅና ንጹሕ ካልሆነ እንስሳ በኵር ሆኖ የተወለደውን ተባዕት ሁሉ ዋጀው።

16. እነዚህም አንድ ወር ሲሆናቸው ሃያ ጌራ በሚመዝነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ፣ በተወሰነው በመዋጃው ዋጋ በአምስት ሰቅል ጥሬ ብር ትዋጀዋለህ።

17. “የተቀደሱ ስለሆኑ የበሬ፣ የበግ ወይም የፍየል በኵር የሆኑትን አትዋጃቸውም፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፤ ሥባቸውንም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ ታቃጥለዋለህ።

18. የሚወዘወዘው ቊርባን ፍርምባና የቀኙ ወርች የአንተ እንደሆነ ሁሉ የእነዚህም ሥጋ የአንተ ይሆናል።

19. እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚያቀርቡት ከተቀደሰ ቊርባን የሚለየው ሁሉ ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለአንተና ለዘሮችህ ዘላለማዊ የጨው ኪዳን ነው።”

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “ከምድራቸው የምትካፈለው ርስት፣ ከእነርሱም የምታገኘው ድርሻ የለህም፤ በእስራኤላውያን መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 18