ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 15:21-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ አንሥታችሁ ይህን ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ትሰጣላችሁ።

22. “ ‘እንግዲህ ካለማወቅ የተነሣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ከሰጣቸው ትእዛዛት አንዱን ሳትፈጽሙ ብትቀሩ፣ ይህም ማለት

23. እግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዛቱን ከሰጠበት ዕለት ጀምሮ በተከታታይ ትውልዶች በሙሴ አማካይነት ያዘዛችሁን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፣

24. ይህም የተፈጸመው ሆን ተብሎ ሳይሆንና ማኅበረ ሰቡም ሳያውቀው ከሆነ፣ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ አድርጎ አንድ ወይፈን በእሳት ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚሁም ጋር ሥርዐቱ የሚጠይቀውን የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ደግሞም ለኀጢአት መሥዋዕት ተባዕት ፍየል ያቅርብ።

25. ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ፤ ምክንያቱም ባለማወቅ የተፈጸመ ስለ ሆነና ስለ ስሕተታቸውም በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) ስላቀረቡ ነው።

26. ባለማወቅ የተደረገውን ስሕተት ሁሉም የፈጸሙት ስለ ሆነ፣ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብና በመካከላቸው የሚኖር መጻተኛ ሁሉ ይቅር ይባላል።

27. “ ‘ነገር ግን አንድ ሰው ካለማወቅ የተነሣ በግሉ ኀጢአት ቢሠራ ግን ለኀጢአት መሥዋዕት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያምጣ።

28. ከዚያም ካህኑ፣ ባለማወቅ ኀጢአት ሠርቶ ለተሣሣተው ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ስርየት በሚደረግለትም ጊዜ ሰውየው ይቅር ይባላል።

29. ያገር ተወላጅ እስራኤላዊ ይሁን ወይም መጻተኛ ባለማወቅ ኀጢአት ከሠራ በማናቸውም ሰው ላይ ሕጉ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።

30. “ ‘ያገር ተወላጅም ይሁን መጻተኛ ሆን ብሎ ኀጢአት የሚሠራ ማንኛውም ሰው ግን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ስለሚያቃልል ያ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ።

31. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ስለናቀ፣ ትእዛዛቱንም ስለ ጣሰ ያ ሰው በእርግጥ ተለይቶ መጥፋት አለበት፤ ጥፋቱ የራሱ ነው።’ ”

32. እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ አንድ ሰው በሰንበት ቀን ዕንጨት ሲለቅም ተገኘ።

33. ዕንጨት ሲለቅም ያገኙትም ሰዎች ሰውየውን ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው የእስራኤል ማኅበር አመጡት፤

34. በሰውየው ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽ የሆነ ነገር ባለመኖሩ በጥበቃ ሥር እንዲቈይ አደረጉት።

35. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ሰውየው ይሙት፤ መላውም ማኅበር ከሰፈር ውጭ በድንጋይ ይውገረው” አለው፤

36. ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ማኅበሩ ሰውየውን ከሰፈር አውጥቶ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገረው።

37. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

38. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ በየልብሳችሁ ጫፍ ላይ ዘርፍ አድርጉ፤ እያንዳንዱም ዘርፍ ሰማያዊ ጥለት ይኑረው።

39. ልባችሁ የተመኘውን፣ ዐይናችሁ ያየውን ሁሉ ተከትላችሁ እንዳታመነዝሩ እነዚህን ዘርፎች በማየት የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዛት በማስታወስ እንድትታዘዙ ማስታወሻ ይሆኑአችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 15