ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 15:15-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ማኅበረ ሰቡ ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ አንድ ዐይነት ደንብ ይኖረዋል፤ ይህም በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ የማይሻር ሥርዐት ነው። እናንተም ሆናችሁ መጻተኞቹ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እኩል ትታያላችሁ፤

16. ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ይኸው ሕግና ሥርዐት እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።’ ”

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

18. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እኔ ወደምወስዳችሁ ምድር ገብታችሁ፣

19. የምድሪቱን በረከት ስትመገቡ ከዚሁ ላይ አንሥታችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊርባን አቅርቡ።

20. ይህንም ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ ኅብስት ጋግራችሁ ከዐውድማ እንደ ተገኘ ቊርባን አድርጋችሁ አምጡ።

21. በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ አንሥታችሁ ይህን ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ትሰጣላችሁ።

22. “ ‘እንግዲህ ካለማወቅ የተነሣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ከሰጣቸው ትእዛዛት አንዱን ሳትፈጽሙ ብትቀሩ፣ ይህም ማለት

23. እግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዛቱን ከሰጠበት ዕለት ጀምሮ በተከታታይ ትውልዶች በሙሴ አማካይነት ያዘዛችሁን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፣

24. ይህም የተፈጸመው ሆን ተብሎ ሳይሆንና ማኅበረ ሰቡም ሳያውቀው ከሆነ፣ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ አድርጎ አንድ ወይፈን በእሳት ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚሁም ጋር ሥርዐቱ የሚጠይቀውን የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ደግሞም ለኀጢአት መሥዋዕት ተባዕት ፍየል ያቅርብ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 15