ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 13:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ሙሴም ከነዓንን እንዲሰልሉ በላካቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ነጌብን ዘልቃችሁ ወደ ተራራማው አገር ግቡ።

18. ምድሪቱ ምን እንደምትመስልና የሚኖሩባትም ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፣ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች መሆናቸውን እዩ።

19. የሚኖሩባት ምድር ምን ዐይነት ናት? መልካም ወይስ መጥፎ? የሚኖሩባቸውስ ከተሞች ምን ይመስላሉ? በግንብ ያልታጠሩ ናቸው ወይስ የተመሸጉ?

20. ዐፈሩስ እንዴት ያለ ነው? ለም ወይስ ደረቅ? ደናም ወይስ ደን አልባ? በተቻለ መጠን ከምድሪቱ ፍሬ ይዛችሁ ኑ። ወቅቱ የወይን ፍሬ መብሰል የጀመረበት ጊዜ ነበር።

21. ስለዚህ ወጥተው ከጺን ምድረ በዳ አንሥቶ በሌቦ ሐማት በኩል እስከ ረአብ ድረስ ዘልቀው ምድሪቱን አጠኑ።

22. በኔጌብ በኩል አልፈው አኪመን፣ ሴሲና ተላሚ የተባሉ የዔናቅ ዝርያዎች ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን መጡ። ኬብሮን የተመሠረተችው ጣኔዎስ በግብፅ ምድር ከመቈርቈሯ ሰባት ዓመት አስቀድሞ ነበር።

23. ወደ ኤሽኮል ሸለቆ በደረሱ ጊዜ የወይን ዘለላ ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ ቈረጡ፤ ይህንንም ከሮማንና ከበለስ ጋር በመሎጊያ አድርገው ለሁለት ተሸከሙት።

24. እስራኤላውያን የወይን ዘለላ ስለ ቈረጡባትም ያች ስፍራ የኤሽኮል ሸለቆ ተባለች።

25. ምድሪቱንም አሥሠው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ።

26. ሰዎቹም፣ ሙሴና አሮን መላውም የእስራኤላውያን ማኅብረ ሰብ ወዳሉበት በፋራን ምድረ በዳ ወደምትገኘው ወደ ቃዴስ ተመለሱ፤ ያዩትንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ አስረዱ፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።

27. ለሙሴም እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “ወደ ላክኸን ምድር ዘልቀን ገባን፤ ማርና ወተት የምታፈስስ ናት፤ ፍሬዋም ይኸው።

28. በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ግን ኀያላን ሲሆኑ፣ ከተሞቹም የተመሸጉና ትላልቅ ናቸው፤ እንዲያውም የዔናቅን ዝርያዎች በዚያ አይተናል።

29. አማሌቃውያን የሚኖሩት በኔጌብ፣ ኬጢያውያን ኢያቡሳውያንና አሞራውያን በኰረብታማው አገር፣ ከነዓናውያን የሚኖሩት ደግሞ በባሕሩ አቅራቢያና በዮርዳኖስ ዳርቻ ነው።”

30. ከዚያም ካሌብ ሕዝቡን በሙሴ ፊት ጸጥ አሰኝቶ፣ “እንውሓ! ምድራቸውን እንውረስ፤ ማሸነፍም እንችላለን” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 13