ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 9:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በስምንተኛውም ቀን ሙሴ አሮንንና ልጆቹን እንዲሁም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራቸው፤

2. አሮንንም እንዲህ አለው፤ “የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ እንቦሳ እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ አውራ በግ፣ ወስደህ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቅርባቸው፤ ሁለቱም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።

3. እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፤ ‘ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት እንከን የሌለባቸውን የአንድ ዓመት እምቦሳና የአንድ ዓመት ጠቦት፣

4. ለኅብረት መሥዋዕት አንድ በሬና አንድ አውራ በግ በዘይት ከተለወሰ የእህል ቊርባን ጋር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመሠዋት አቅርቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ ይገለጥላችኋልና።’ ”

5. እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ሕዝቡም በሙሉ ቀርበው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሙ።

6. ሙሴም፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር ይገለጥላችሁ ዘንድ፣ እንድታደርጉት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዛችሁ ይህ ነው” አለ።

7. ሙሴ አሮንን፣ ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኀጢአት መሥዋዕትህንና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፤ ለራስህና ለሕዝቡም አስተሰርይ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት የሕዝቡን መሥዋዕት አቅርብ፤ አስተሰርይላቸውም” አለው።

8. አሮንም ወደ መሠዊያው መጥቶ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት የቀረበውን እምቦሳ ዐረደው።

9. ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ግርጌ አፈሰሰው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 9