ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 8:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሙሴም አሮንንና ልጆቹን ወደ ፊት አወጣቸው፤ በውሃም አጠባቸው።

7. አሮንን እጀ ጠባብ አለበሰው፤ መቀነት አስታጠቀው፤ ቀሚስ አጠለቀለት፤ ኤፉድ ደረበለት፤ በልዩ ጥበብ በተጠለፈው መታጠቂያ ኤፉዱን አስታጠቀው፤ በላዩም አሰረው፤

8. የደረት ኪሱን በላዩ አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረ።

9. እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘውም መሠረት፣ ሙሴ ጥምጥሙን በአሮን ራስ ላይ አደረገ፤ በጥምጥሙም ላይ በፊት ለፊቱ በኩል የተቀደሰውን አክሊል አደረገለት።

10. ሙሴም መቅቢያ ዘይቱን ወሰደ፤ ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሰ።

11. ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድ ሳቸውም ዘንድ መሠዊያውን ከነመገልገያ ዕቃው ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሳሕኑን ከነማስቀመጫው በዘይት ቀባ።

12. ከመቅቢያ ዘይቱም በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ የተቀደሰ እንዲሆንም ቀባው።

13. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ሙሴ፣ የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ እጀ ጠባብ አለበሳቸው፤ መታጠቂያ አስታጠቃቸው፤ ቆብም ደፋላቸው።

14. ሙሴም የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ወይፈን አመጣ፤ አሮንና ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ።

15. ሙሴም ወይፈኑን ዐረደ፤ ደሙንም ወስዶ መሠዊያውን ያነጻ ዘንድ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ቀባ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው። ለመሠዊያውም እንዲህ አድርጎ ያስተሰርይለት ዘንድ ቀደሰው።

16. ሙሴም የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሁሉ፣ የጒበቱን ሽፋን፣ ኵላሊቶችንና ሥባቸውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ።

17. ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ወይፈኑን፣ ቈዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጠለ።

18. ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጃቸውን በበጉ ላይ ጫኑ።

19. ሙሴም በጉን ዐርዶ ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ።

20. በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ።

21. ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 8