ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 6:14-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. “ ‘የእህል ቊርባን ሥርዐት ይህ ነው፦ የአሮን ልጆች ቊርባኑን በመሠዊያው ትይዩ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርቡት።

15. ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ያንሣለት፤ በእህሉ ቊርባን ላይ ያለውንም ዕጣን በሙሉ ይውሰድ፤ ይህንም፣ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ፣ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው።

16. የተረፈውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ እርሾ ሳይገባበት በተቀደሰው ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ አደባባዩ ላይ ይብሉት።

17. ያለ እርሾ መጋገር አለበት፤ በእሳት ከሚቀርብልኝ ቊርባን ይህን የእነርሱ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም፣ እንደ ኀጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ነው።

18. ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለእርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’ ”

19. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

20. “አሮን ወይም ልጆቹ በተቀቡበት ዕለት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡት ቊርባን ይህ ነው፦ የኢፍ አንድ ዐሥረኛው የላመ ዱቄት ግማሹን ለጧት፣ ግማሹን ለማታ የዘወትር የእህል ቊርባን አድርገው ያቅርቡት።

21. በሚገባ በዘይት ተለውሶ በምጣድ ላይ ይጋገር፤ ከዚያም የእህሉን ቊርባን ቈራርሰህ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ አቅርብ።

22. በእርሱ ቦታ ተቀብቶ ካህን የሚሆነው ልጁ ይህን ያዘጋጅ፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተመደበ ድርሻ ነውና ፈጽሞ ይቃጠል።

23. ካህኑ የሚያቀርበው የእህል ቊርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠል እንጂ አይበላ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 6