ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 23:33-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

33. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

34. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሰባተኛውም ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) የዳስ በዓል ይጀምራል፤ እስከ ሰባት ቀንም ይቆያል።

35. የመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነውና የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።

36. ሰባት ቀን መሥዋዕቱን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑበት።

37. “ ‘የሚቃጠል መሥዋዕትንና የእህል ቊርባንን፣ መሥዋዕትንና የመጠጥ ቊርባንን በተመደበላቸው ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ለማቅረብ፣ የተቀደሱ ጉባኤዎችን የምታውጁባቸው የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት እነዚህ ናቸው።

38. እነዚህ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ከምታቀርቡት፣ ከስጦታችሁ፣ ከስእለታችሁና ከበጎ ፈቃድ ስጦታችሁ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ስጦታዎች ናቸው።

39. “ ‘የምድራችሁን ፍሬ ከሰበሰባችሁ በኋላ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምራችሁ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አክብሩ፤ የመጀመሪያው ቀን የዕረፍት ዕለት ነው፤ ስምንተኛውም ቀን እንደዚሁ የዕረፍት ዕለት ይሆናል።

40. በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የለመለመ ዛፍ ቅርንጫፍ የአኻያ ዛፍ ቅርንጫፍ ይዛችሁ ሰባት ቀን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበላችሁ።

41. በየዓመቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ሰባት ቀን አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው፤ በሰባተኛውም ወር አክብሩት።

42. ሰባት ቀን ዳስ ውስጥ ተቀመጡ፤ በትውልዱ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ ዳስ ውስጥ ይሰንብት፤

43. በዚህም እኔ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባወጣሁ ጊዜ፣ ዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’ ”

44. በዚህ ሁኔታም ሙሴ የተመረጡትን የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት ለእስራኤላውያን አስታወቀ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 23