ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 23:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2. “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምትዋጇቸው የተመረጡ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት እነዚህ ናቸው፤

3. “ ‘ሥራ የምትሠሩበት ስድስት ቀን አላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት፣ የተቀደሰ ጉባኤ ዕለት ነው። የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ስለ ሆነ፣ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩበት።

4. “ ‘የተመረጡ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት ብላችሁ በተወሰኑላቸው ጊዜያት የምታውጇቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እነዚህ ናቸው፤

5. የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ በዓል ይጀመራል።

6. በዚያው ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) የቂጣ በዓል ይጀመራል፤ ሰባት ቀንም ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ትበላላችሁ።

7. በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዕለት ተግባራችሁንም አታከናውኑ።

8. ሰባት ቀን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ በዚያ ዕለት የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑ።’ ”

9. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

10. “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ከሰበሰባችሁት እህል የመጀመሪያውን ነዶ ለካህኑ አቅርቡ፤

11. ነዶው ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዘው፤ ካህኑ ነዶውን የሚወዘውዘው በሰንበት ቀን ማግስት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 23