ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 19:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. “ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም፤“ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።

14. “ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

15. “ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታዳላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በትክክል ፍረድ።

16. “ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ፤“ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

17. “ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው።

18. “ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

19. “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤“ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል፤“ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤“ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።

20. “ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም።

21. ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያምጣ።

22. ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።

23. “ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት የተከለከለ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ በመሆኑ አይበላ።

24. በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 19