ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 19:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2. “ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።

3. “ ‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

4. “ ‘ወደ ጣዖታት ዘወር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክት አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

5. “ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ።

6. መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግሥቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል።

7. በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም።

8. ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።

9. “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በእርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ።

10. የወይንህን እርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

11. “ ‘አትስረቁ፤“ ‘አትዋሹ፤“ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታል።

12. “ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን (ኤሎሂም) ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

13. “ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም፤“ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።

14. “ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 19