ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 14:5-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ካህኑም ከወፎቹ አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ።

6. በሕይወት ያለውንም ወፍ ከዝግባው ዕንጨት፣ ደመቅ ካለው ቀይ ድርና ከሂሶጵ ጋር በምንጩ ውሃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከር።

7. ከተላላፊ በሽታ የሚነጻውንም ሰው ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ መንጻቱንም ያስታውቅ፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ውጭ ይልቀቀው።

8. “የሚነጻው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ጠጒሩን በሙሉ ይላጭ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ ይሆናል። ከዚህም በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል፤ ነገር ግን ሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቈይ።

9. በሰባተኛውም ቀን ጠጒሩን በሙሉ ይላጭ፤ ራሱን፣ ጢሙን፣ ቅንድቡንና ሌላውንም ጠጒር ሁሉ ይላጭ። ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።

10. “በስምንተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለባትን አንዲት የዓመት እንስት በግ ያቅርብ፤ እንዲሁም ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ያቅርብ፤ ደግሞ አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ።

11. ሰውየው የነጻ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህን የሚነጻውን ሰውና መሥዋዕቶቹን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ።

12. “ካህኑም ከተባዕቱ ጠቦቶች በመውሰድ ከሎግ ዘይቱ ጋር የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዛቸው።

13. ጠቦቱንም፣ የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት በተቀደሰው ስፍራ ይረደው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱ ለካህኑ እንደሚሰጥ ሁሉ የበደል መሥዋዕቱም ለካህኑ ይሰጥ፤ ይህም እጅግ የተቀደሰ ነው።

14. ካህኑ ከበደል መሥዋዕቱ ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ።

15. ካህኑም ከሎግ ዘይት ወስዶ በራሱ ግራ እጅ መዳፍ ውስጥ ይጨምር፤

16. የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይርጭ።

17. ካህኑ በመዳፉ ውስጥ ከቀረው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት በበደል መሥዋዕቱ ደም ላይ ደርቦ ይቅባ።

18. በመዳፉ ላይ የቀረውንም ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያድርግ፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለት።

19. “ካህኑም የኀጢአት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከርኵሰቱ ለሚነጻውም ሰው ያስተሰርይለት፤ ከዚህ በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ይረድ፤

20. ከእህል ቊርባኑም ጋር በመሠዊያው ላይ በማቅረብ ያስተሰርይለት፤ ሰውየውም ንጹሕ ይሆናል።

21. “ሰውየው ድኻ ከሆነና እነዚህን ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደለት፣ ማስተሰረያ እንዲሆነው የሚወዘወዝ አንድ ተባዕት የበግ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፣ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለእህል ቊርባን ያቅርብ፤ ደግሞም አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 14