ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 13:31-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. ካህኑ እንዲህ ዐይነቱን ቊስል በሚመረምርበት ጊዜ፣ ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባና በውስጡም ጥቊር ጠጒር ከሌለ፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው።

32. ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቊስሉን ይመርምር፤ የሚያሳክከው ቦታ ያልሰፋ፣ ቢጫ ጠጒር የሌለውና ከቈዳው በታች ዘልቆ ያልገባ ከሆነ፣

33. ከቈሰለው ቦታ በስተቀር ጠጒሩን ይላጭ፤ ካህኑ ሰባት ተጨማሪ ቀን ሰውየውን ያግልል።

34. ካህኑ በሰባተኛው ቀን የሚያሳክከውን የሰውየውን ቊስል ይመርምር፤ በቈዳው ላይ ካልሰፋና ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባ ካህኑ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሁን።

35. ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ግን የሚያሳክከው ቊስል ተስፋፍቶ ቢገኝ፣

36. ካህኑ ይመርምረው፤ ቊስሉ በቈዳው ላይ ከሰፋ፣ ካህኑ የጠጒሩን ቢጫ መሆን አለመሆን ማየት አያሻውም፤ ሰውየው ርኩስ ነው።

37. ነገር ግን ቊስሉ በካህኑ አመለካከት ለውጥ ያላሳየ ከሆነና በውስጡ ጥቊር ጠጒር ካበቀለ ቊስሉ ድኖአል፤ ሰውየው ነጽቶአል፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ።

38. “በወንድ ወይም በሴት ቈዳ ላይ ቋቍቻ ቢወጣ፣

39. ካህኑ ይመርምራቸው፤ ቋቍቻው ዳለቻ ከሆነ በቈዳ ላይ የወጣ ጒዳት የማያስከትል ችፍታ ነው፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው።

40. “አንድ ሰው የራሱ ጠጒር ከዐናቱ አልቆ መላጣ ቢሆን ንጹሕ ነው።

41. ጠጒሩ ከፊት ለፊት ተመልጦ ራሰ በራ ቢሆንም ንጹሕ ነው።

42. ነገር ግን በመላጣው ወይም በበራው ላይ ነጣ ያለ ቀይ ቊስል ቢወጣበት፣ ያ ከመላጣው ወይም ከበራው የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው።

43. ካህኑ ይመርምረው፤ በመላጣው ወይም በበራው ላይ ያበጠው ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚመስል ነጣ ያለ ቊስል ከሆነ፣

44. ሰውየው ደዌ አለበት፤ ርኵስም ነው፤ በራሱ ላይ ካለው ቊስል የተነሣም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 13