ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 11:31-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሁሉ መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ ከእነዚህም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

32. በድኑ በማንኛውም ዕቃ ላይ ቢወድቅ ያ ዕቃ ከዕንጨት፣ ከጨርቅ፣ ከቈዳ ወይም ከበርኖስ የተሠራ ቢሆን ርኩስ ይሆናል፤ በውሃ ውስጥ ይደረግ፤ ሆኖም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።

33. በድኑም በሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፣ በውስጡ ያለ ነገር ሁሉ ርኩስ ስለሚሆን ዕቃውን ስበሩት።

34. ማንኛውም ምግብ እንዲህ ካለው ዕቃ ውሃ ቢፈስበት ይረክሳል፤ ከዚህ ዕቃ የሚጠጣውም ነገር ሁሉ ርኵስ ነው፤

35. ከበድናቸው አንዱ የወደቀበት ነገር ሁሉ ይረክሳል፤ ምድጃም ይሁን ማሰሮ ይሰበር፤ ርኩሳን ናቸው፤ እናንተም ተጸየፏቸው።

36. ነገር ግን ምንጭ ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ንጹሕ እንደሆነ ይቈያል፤ ሆኖም በድኑን የነካ ይረክሳል።

37. በሚዘራ ዘር ላይ በድን ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ እንደሆነ ይቆያል።

38. ነገር ግን በዘሩ ላይ ውሃ ከፈሰሰበት በኋላ በድን ቢወድቅበት ዘሩ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።

39. “ ‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳት አንዱ ቢሞት፣ በድኑን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

40. ማንም ሰው ከበድኑ ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ በድኑን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

41. “ ‘ምድር ለምድር የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡር ጸያፍ ነው፤ አይበላም።

42. ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጡር ሁሉ፣ ይኸውም በደረቱ የሚሳበውን ወይም በአራት እግር የሚሄደውን ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን አትብሉ፤ ጸያፍ ነው።

43. በእነዚህ ፍጡራን ሁሉ ራሳችሁን አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነርሱም ራሳችሁን በማጒደፍ አትርከሱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 11