ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የተፈቀደና ያልተፈቀደ መብል

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

2. “እስራኤላውያንን እንዲህ በሏቸው፤ ‘በየብስ ከሚኖሩ እንስሳት ሁሉ የምትበሏቸው እነዚህ ናቸው፦

3. ሰኰናው የተሰነጠቀውን የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ መብላት ትችላላችሁ።

4. “ ‘የሚያመሰኩ ሆነው ሰኰናቸው ያልተሰነጠቀ ወይም ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ሆኖ የማያመሰኩትን አትብሉ፤ ግመል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

5. ሽኮኮ ያመስኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

6. ጥንቸል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

7. ዐሳማ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

8. የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ፤ ጥንባቸውንም አትንኩ፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሁኑ።

9. “ ‘በባሕሮችና በወንዞች ውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ፍጡሮች ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን መብላት ትችላላችሁ፤

10. ነገር ግን በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ከሚኖሩት ፍጡሮች ሁሉ፣ ከሚንፏ ቀቁት ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ሕይወት ካላቸው ሌሎች ፍጡሮች መካከል ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ፤

11. በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ስለሆኑ ሥጋቸውን አትብሉ፤ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ፤

12. ክንፍና ቅርፊት የሌለው ማንኛውም በውሃ ውስጥ የሚኖር ፍጡር በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ይሁን።

13. “ ‘ከአዕዋፍ ወገን እነዚህን ትጸየፋላችሁ፤ ጸያፍ ስለ ሆኑም አትብሏቸው፦ ንስር፣ ጥንብ አንሣ፣ ግልገል አንሣ፣

14. ጭላት፣ ማንኛውም ዐይነት ጭልፊት፣

15. ማንኛውም ዐይነት ቊራ፣

16. ሰጐን፣ ጠላቋ፣ ዝይ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣

17. ጒጒት፣ ርኩም፣ ጋጋኖ፣

18. የውሃ ዶሮ፣ ይብራ፣ ስደተኛ አሞራ፣

19. ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ።

20. “ ‘ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ።

21. ነገር ግን ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር ከሚንቀሳቀሱ ነፍሳት መካከል ከምድር በሚፈናጠሩበት እግራቸው አንጓ ያለባቸውን መብላት ትችላላችሁ።

22. ከእነዚህ ማንኛውንም ዐይነት አንበጣ፣ ፌንጣና ኵብኵባ መብላት ትችላላችሁ።

23. ነገር ግን ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ተጸየፏቸው።

24. “ ‘ከእነዚህ የተነሣ ትረክሳላችሁ፤ የእነዚህን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኵስ ይሆናል።

25. የእነዚህንም በድን የሚያነሣ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።

26. “ ‘ሰኰና ያለው፣ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። የእነዚህንም በድን የሚነካ ሰው ሁሉ ይረክሳል።

27. አራት እግር ካላቸው እንስሳት ሁሉ በመዳፋቸው የሚሄዱት በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ በድናቸውንም የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኵስ ይሆናል።

28. የእነዚህን በድን የሚያነሣ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እንስሳቱም በእናንተ ዘንድ ርኵሳን ናቸው።

29. “ ‘ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፦ ሙጭልጭላ፣ ዐይጥ፣ እንሽላሊት በየወገኑ፣

30. ዔሊ፣ ዐዞ፣ ገበሎ፣ አርጃኖ፣ ዕሥሥት።

31. ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሁሉ መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ ከእነዚህም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

32. በድኑ በማንኛውም ዕቃ ላይ ቢወድቅ ያ ዕቃ ከዕንጨት፣ ከጨርቅ፣ ከቈዳ ወይም ከበርኖስ የተሠራ ቢሆን ርኩስ ይሆናል፤ በውሃ ውስጥ ይደረግ፤ ሆኖም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።

33. በድኑም በሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፣ በውስጡ ያለ ነገር ሁሉ ርኩስ ስለሚሆን ዕቃውን ስበሩት።

34. ማንኛውም ምግብ እንዲህ ካለው ዕቃ ውሃ ቢፈስበት ይረክሳል፤ ከዚህ ዕቃ የሚጠጣውም ነገር ሁሉ ርኵስ ነው፤

35. ከበድናቸው አንዱ የወደቀበት ነገር ሁሉ ይረክሳል፤ ምድጃም ይሁን ማሰሮ ይሰበር፤ ርኩሳን ናቸው፤ እናንተም ተጸየፏቸው።

36. ነገር ግን ምንጭ ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ንጹሕ እንደሆነ ይቈያል፤ ሆኖም በድኑን የነካ ይረክሳል።

37. በሚዘራ ዘር ላይ በድን ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ እንደሆነ ይቆያል።

38. ነገር ግን በዘሩ ላይ ውሃ ከፈሰሰበት በኋላ በድን ቢወድቅበት ዘሩ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።

39. “ ‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳት አንዱ ቢሞት፣ በድኑን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

40. ማንም ሰው ከበድኑ ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ በድኑን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

41. “ ‘ምድር ለምድር የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡር ጸያፍ ነው፤ አይበላም።

42. ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጡር ሁሉ፣ ይኸውም በደረቱ የሚሳበውን ወይም በአራት እግር የሚሄደውን ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን አትብሉ፤ ጸያፍ ነው።

43. በእነዚህ ፍጡራን ሁሉ ራሳችሁን አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነርሱም ራሳችሁን በማጒደፍ አትርከሱ።

44. እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ተለዩ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ ምድር ለምድር በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ፍጡር ራሳችሁን አታርክሱ።

45. አምላካችሁ (ኤሎሂም) እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።

46. “ ‘እንስሳትንና አዕዋፍን፣ በውሃ ውስጥ የሚኖሩትንና ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ሁሉ በሚመለከት የተሰጠ ሕግ ይህ ነው።

47. በዚህም በርኩሱና በንጹሑ መካከል፣ እንዲሁም ሕይወት ካላቸው ፍጡራን የሚበሉትንና የማይበሉትን ትለያላችሁ።’ ”