ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 8:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ከአዶኒቃም ዘሮች፣ የመጨረሻዎቹ ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፋላት፣ ይዑኤልና ሸማያ፣ ከእነርሱም ጋር 60 ወንዶች፤

14. ከበጉዋይ ዘሮች ዑታይና ዘቡድ፣ ከእነርሱም ጋር 70 ወንዶች።

15. እኔም ወደ አኅዋ በሚፈሰው ወንዝ አጠገብ ሰዎቹን ሰበሰብኋቸው፤ በዚያም ሦስት ቀን ቈየን፤ ሕዝቡንና ካህናቱን ስመለከት፣ ከሌዊ ወገን የሆነ አንድም ሰው በዚያ አላገኘሁም።

16. ስለዚህ መራሕያኑን አልዓዛርን፣ አርኤልን፣ ሸማያን፣ ኤልናታንን፣ ያሪብን፣ ኤልናታን፣ ናታንን፣ ዘካርያስንና ሜሱላምን እንዲሁም መምህራኑን ዮያሪብንና ኤልናታንን አስጠራኋቸው፤

17. እነርሱንም ካሲፍያ በሚባል ስፍራ አለቃ ወደ ሆነው ወደ አዶ ላክኋቸው፤ በአምላካችን ቤት የሚያገለግሉ ሰዎችን ያመጡልን ዘንድ በካሲፍያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ለሆኑት ለአዶና ለሥጋ ዘመዶቹ የሚናገሩትን አስታወቅኋቸው።

18. መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በእኛ ላይ ስለ ነበረች፣ ከሞሖሊ ዘሮች የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ የሆነውን ሰራብያ ተብሎ የሚጠራውን አስተዋይ ሰው፣ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንት የሚሆኑ ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን፤

19. እንዲሁም ሐሸብያንና ከሜራሪ ዘሮች የሻያን፣ ከወንድሞቹና ከአጎቶቹ ወንዶች ልጆች ጋር 20 ወንዶችን አመጡልን።

20. በተጨማሪም ዳዊትና ሹማምቱ ሌዋውያኑን እንዲረዳ ካቋቋሙት ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ቡድን 220 አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየስማቸው ተመዘገቡ።

21. ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጒዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ።

22. “መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቊጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር።

23. ስለዚህ ጾምን፤ ወደ አምላካችንም ስለዚህ ነገር ልመና አቀረብን፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ።

24. እኔም ከዋና ዋናዎቹ ካህናትም ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፣ ከእነርሱም ጋር ሰራብያን፣ ሐሸቢያንና ከወንድሞቻቸውም መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ፤

25. ንጉሡ፣ አማካሪዎቹ፣ ሹሞቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን ብር፣ ወርቅና ዕቃ ሁሉ መዝኜ ሰጠኋቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 8