ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዕዝራ ጋር የተመለሱት የየቤተ ሰቡ አለቆች ስም ዝርዝር

1. በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት ከባቢሎን አብረውኝ የወጡት የየቤተ ሰቡ አለቆችና አብረዋቸው የተመዘገቡት እነዚህ ናቸው፤

2. ከፊንሐስ ዘሮች ጌርሶን፤ከኢታምር ዘሮች ዳንኤል፤ከዳዊት ዘሮች ሐጡስ፤

3. እርሱም ከሴኬንያ ዘሮች ነው፤ከፋሮስ ዘሮች ዘካርያስና ከእርሱም ጋር 150 ወንዶች ተመዝግበው ነበር፤

4. ከፋሐት ሞዓብ ዘሮች የዘራእያ ልጅ ኤሊሆ ዔናይና ከእርሱም ጋር 200 ወንዶች፤

5. ከዛቱ ዘሮች የየሕዚኤል ልጅ ሴኬንያና ከእርሱም ጋር 300 ወንዶች፤

6. ከዓዲን ዘሮች የዮናታን ልጅ ዔቤድና ከእርሱም ጋር 50 ወንዶች፤

7. ከኤላም ዘሮች የጎቶልያ ልጅ የሻያና ከእርሱም ጋር 70 ወንዶች፤

8. ከሰፋጥያስ ዘሮች፣ የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፣ ከ80 ወንዶች ጋር፤

9. ከኢዮአብ ዘሮች የይሒኤል ልጅ አብድዩና ከእርሱ ጋር 218 ወንዶች፤

10. ከባኒ ዘሮች የዮሲፍያ ልጅ ሰሎሚትና ከእርሱም ጋር 160 ወንዶች፤

11. ከቤባይ ዘሮች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ ከእርሱም ጋር 28 ወንዶች፤

12. ከዓዝጋድ ዘሮች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናንና ከእርሱም ጋር 110 ወንዶች፤

13. ከአዶኒቃም ዘሮች፣ የመጨረሻዎቹ ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፋላት፣ ይዑኤልና ሸማያ፣ ከእነርሱም ጋር 60 ወንዶች፤

14. ከበጉዋይ ዘሮች ዑታይና ዘቡድ፣ ከእነርሱም ጋር 70 ወንዶች።

ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ

15. እኔም ወደ አኅዋ በሚፈሰው ወንዝ አጠገብ ሰዎቹን ሰበሰብኋቸው፤ በዚያም ሦስት ቀን ቈየን፤ ሕዝቡንና ካህናቱን ስመለከት፣ ከሌዊ ወገን የሆነ አንድም ሰው በዚያ አላገኘሁም።

16. ስለዚህ መራሕያኑን አልዓዛርን፣ አርኤልን፣ ሸማያን፣ ኤልናታንን፣ ያሪብን፣ ኤልናታን፣ ናታንን፣ ዘካርያስንና ሜሱላምን እንዲሁም መምህራኑን ዮያሪብንና ኤልናታንን አስጠራኋቸው፤

17. እነርሱንም ካሲፍያ በሚባል ስፍራ አለቃ ወደ ሆነው ወደ አዶ ላክኋቸው፤ በአምላካችን ቤት የሚያገለግሉ ሰዎችን ያመጡልን ዘንድ በካሲፍያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ለሆኑት ለአዶና ለሥጋ ዘመዶቹ የሚናገሩትን አስታወቅኋቸው።

18. መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በእኛ ላይ ስለ ነበረች፣ ከሞሖሊ ዘሮች የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ የሆነውን ሰራብያ ተብሎ የሚጠራውን አስተዋይ ሰው፣ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንት የሚሆኑ ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን፤

19. እንዲሁም ሐሸብያንና ከሜራሪ ዘሮች የሻያን፣ ከወንድሞቹና ከአጎቶቹ ወንዶች ልጆች ጋር 20 ወንዶችን አመጡልን።

20. በተጨማሪም ዳዊትና ሹማምቱ ሌዋውያኑን እንዲረዳ ካቋቋሙት ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ቡድን 220 አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየስማቸው ተመዘገቡ።

21. ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጒዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ።

22. “መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቊጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር።

23. ስለዚህ ጾምን፤ ወደ አምላካችንም ስለዚህ ነገር ልመና አቀረብን፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ።

24. እኔም ከዋና ዋናዎቹ ካህናትም ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፣ ከእነርሱም ጋር ሰራብያን፣ ሐሸቢያንና ከወንድሞቻቸውም መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ፤

25. ንጉሡ፣ አማካሪዎቹ፣ ሹሞቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን ብር፣ ወርቅና ዕቃ ሁሉ መዝኜ ሰጠኋቸው።

26. ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብር፣ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፣ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፣

27. አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ ሃያ የወርቅ ወጭቶችና እንደ ወርቅ ነጥረው ከሚያብረቀርቅ ናስ የተሠሩ ሁለት ዕቃዎችን መዝኜ በእጃቸው አስረከብኋቸው።

28. እንዲህም አልኋቸው፤ “እናንተና እነዚህ ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ብሩና ወርቁ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር በበጎ ፈቃድ የቀረበ መባ ነው።

29. ኢየሩሳሌም በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤት ክፍሎች ውስጥ በዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ በሌዋውያኑና በየቤተ ሰቡ የእስራኤል አለቆች ፊት እስክትመዝኗቸው ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።”

30. ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ አምላካችን ቤት እንዲሄድ የተመዘነውን ብር፣ ወርቅና ንዋያተ ቅድሳት ተረከቡ።

31. እኛም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችን እጅ በላያችን ነበረች፤ እርሱም ከጠላቶቻችንና በመንገድ ላይ ከሚሸምቁ አዳነን።

32. ኢየሩሳሌምም ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ዐረፍን።

33. በአራተኛው ቀን ብሩን፣ ወርቁንና ንዋያተ ቅድሳቱን በአምላካችን ቤት መዝነን ለኦሪዮ ልጅ ለካህኑ ለሜሪሞት በእጁ አስረከብነው፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር፣ ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ።

34. ሁሉም ነገር ተቈጠረ፤ ተመዘነም፤ የተመዘነውም ሁሉ በዚያኑ ጊዜ ተመዘገበ።

35. ከዚያም ከምርኮ የተመለሱት፣ ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፣ ዘጠና ስድስት አውራ በጎችን፣ ሰባ ሰባት ተባዕት ጠቦቶችን፣ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ለእግዚአብሔር የቀረበ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበር።

36. የንጉሡንም ትእዛዝ ለንጉሡ እንደራሴዎችና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት አገረ ገዦች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት ረዱ።