ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 7:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ከዚህም በላይ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ለመስጠት የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ግምጃ ቤት መውሰድ ትችላለህ።

21. በኤፍራጥስ ማዶ የምትገኙ በጅሮንዶች ሁሉ፣ የሰማይ አምላክ ሕግ መምህር የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት እኔ ንጉሥ አርጤክስስ እነሆ አዝዣለሁ፤

22. እስከ አንድ መቶ መክሊት ብር፣ እስከ አንድ መቶ ቆሮስ ስንዴ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ የወይራ ዘይትና የሚፈለገውን ያህል ጨው ስጡት።

23. የሰማይ አምላክ የሚያዘው ሁሉ፣ ለሰማይ አምላክ ቤተ መቅደስ በፍጹም ትጋት ይደረግ፤ በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ለምን ቊጣ ይውረድ?

24. ደግሞም በካህናቱ፣ በሌዋውያኑ፣ በመዘምራኑ፣ በበር ጠባቂዎቹ፣ በቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ወይም በሌሎቹ በዚህ በእግዚአብሔር ቤት ሠራተኞች ላይ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻ ለመጣል ሥልጣን እንደ ሌላችሁ ይህን ዕወቁ።

25. አንተም ዕዝራ ከአምላክህ እንደ ተሰጠህ ጥበብ መጠን፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ የአምላክህን ሕግ የሚያውቁ ዳኞችንና ፈራጆችን ሹምላቸው፤ ሕጉን የማያውቅ ሰው ቢኖር፣ አንተ ራስህ አስተምረው።

26. ለአምላክህ ሕግና ለንጉሡ ሕግ የማይታዘዝ ማንኛውም ሰው፣ የሞት ወይም የስደት ወይም የንብረት መወረስ ወይም የእስራት ቅጣት ይፈጸምበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 7