ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 7:22-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ስለ መሥዋዕቶችና ስለሚቃጠል መሥዋዕት አልተናገርኋቸውም፤ ትእዛዝም አልሰጠኋቸውም።

23. ነገር ግን ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ መልካም እንዲሆንላችሁም፣ ባዘዝዃችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ አዘዝኋቸው።

24. እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብ ብለው ለማድመጥም አልፈለጉም፤ ይልቁን የክፉ ልባቸውን ሐሳብ በእልኸኝነት ተከተሉ፤ ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላቸው ተመለሱ።

25. አባቶቻችሁ ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በየቀኑ ሳላሰልስ አገልጋዮቼን ነቢያትን ላክሁባቸው።

26. ሕዝቡ ግን አልሰማኝም፤ ልብ ብሎ ለማድመጥም አልፈለገም፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ አባቶቻቸው ከሠሩት የባሰም ክፉ አደረጉ።” ’

27. “ይህን ሁሉ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱ ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፤ አይመል ሱልህም።

28. ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ይህ ሕዝብ አምላኩን እግዚአብሔርን ያልታዘዘ፣ ምክሩን ያልተቀበለ ወገን ነው፤ እውነት ጠፍቶአል፤ ከአንደበታቸውም ሸሽቶአል።

29. እግዚአብሔር ቍጣው የወረደበትን ይህን ትውልድ ስለ ናቀውና ስለ ተወው፣ ጠጒርሽን ቈርጠሽ ጣይ፤ በባድሞቹ ኰረብቶች ላይ ሆነሽም ሙሾ አውጪ።

30. “ ‘የይሁዳ ሕዝብ በፊቴ ክፉ ነገር አድርጓል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ አስጸያፊ ነገራቸውን ስሜ በተጠራበት ቤት በማስቀመጥ አርክሰውታል።

31. እኔ ያላዘዝኋቸውን፣ ከቶም ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለመሠዋት በሄኖም ልጅ ሸለቆ የቶፌትን መስገጃ ኰረብቶች ሠሩ።

32. ስለዚህ አስተውሉ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ስፍራ እስከማይገኝ ድረስ ሙታንን በቶፌት ስለሚቀ ብሩ፣ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ተብሎ የማይጠራበት ጊዜ ይመጣል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 7