ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 52:20-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከናስ ያሠራቸው፦ ሁለቱ ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፣ ከሥሩ ያሉት ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችና ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ሚዛን ከሚችለው በላይ ነበር።

21. እያንዳንዱም ዐምድ ከፍ ታውዐሥራ ስምንት ክንድ ዙሪያ ክቡም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውስጡ ክፍት ስለ ሆነ የእያንዳንዱ ከንፈር ውፍረት አራት ጣት ነበረ።

22. በአንዱ ዐምድ ዐናት ላይ ያለው የናስ ጒልላት ቁመት አምስት ክንድ ሲሆን፣ ዙሪያውንም ሁሉ የሮማን ቅርጽ ባላቸው የናስ ጌጣጌጦች የተዋበ ነበር፤ ሌላውም ዐምድ የሮማኑን ጌጣጌጥ ጨምሮ ከዚሁ ጋር አንድ ዐይነት ነበር።

23. ዘጠና ስድስቱ ሮማኖች ከጐን በቀላሉ የሚታዩ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ በዙሪያው ካለው ጌጥ በላይ ያለው የሮማኖች ቍጥር አንድ መቶ ነበር።

24. የክብር ዘበኞቹ አዛዥ የካህናት አለቃ የነበረውን ሠራያን፣ ምክትሉንም ካህን ሶፎንያስንና ሦስቱን በር ጠባቂዎች አስሮ ወሰዳቸው፤

25. በከተማው ውስጥ ከቀሩትም ሕዝብ፣ የተዋጊዎቹ ኀላፊ የነበረውን መኰንን፣ ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች ከአገሬው ሕዝብ ወታደር የሚመለምለውን መኰንን ጸሓፊና በከተማው ውስጥ የተገኙትን ሌሎች ስድሳ ሰዎች ወሰደ።

26. የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ የባቢሎን ንጉሥ ወደነበረበት ወደ ሪብላ አመጣቸው።

27. ንጉሡም በሐማት ምድር በነበረችው በሪብላ ፈጃቸው።ይሁዳም በዚህ ሁኔታ ከምድሯ በምርኮ ተወሰደች።

28. ናቡከደነፆር ማርኮ የወሰደው ሕዝብ ቍጥር እንደሚከተለው ነው፦በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ሦስት ሺህ ሃያ ሦስት አይሁድ፤

29. ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራስምንተኛው ዓመት፣ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 52