ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 52:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. የዘቦቹ አዛዥ ናቡዘረዳን አንዳንድ ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ፣ የእጅ ጥበብ ያላቸውንና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን አፈለሳቸው።

16. ነገር ግን የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን ሌሎች የምድሪቱን ድኾች ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው።

17. ባቢሎናውያን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፣ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ገንዳ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ይዘው ሄዱ።

18. ከእነዚህም ሌላ ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ወጭቶችን፣ ጭልፋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የናስ ዕቃዎች በሙሉ ወሰዱ።

19. የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ከንጹሕ ወርቅና ከንጹሕ ብር የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ጐድጓዳ ሳሕኖችን ጥናዎችን፣ ወጭቶችን፣ ምንቸቶችን፣ መቅረዞችን፣ ጭልፋዎችንና ለመጠጥ ቍርባን ማቅረቢያ የሚሆኑ ወጭቶችን ይዞ ሄደ።

20. ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከናስ ያሠራቸው፦ ሁለቱ ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፣ ከሥሩ ያሉት ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችና ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ሚዛን ከሚችለው በላይ ነበር።

21. እያንዳንዱም ዐምድ ከፍ ታውዐሥራ ስምንት ክንድ ዙሪያ ክቡም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውስጡ ክፍት ስለ ሆነ የእያንዳንዱ ከንፈር ውፍረት አራት ጣት ነበረ።

22. በአንዱ ዐምድ ዐናት ላይ ያለው የናስ ጒልላት ቁመት አምስት ክንድ ሲሆን፣ ዙሪያውንም ሁሉ የሮማን ቅርጽ ባላቸው የናስ ጌጣጌጦች የተዋበ ነበር፤ ሌላውም ዐምድ የሮማኑን ጌጣጌጥ ጨምሮ ከዚሁ ጋር አንድ ዐይነት ነበር።

23. ዘጠና ስድስቱ ሮማኖች ከጐን በቀላሉ የሚታዩ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ በዙሪያው ካለው ጌጥ በላይ ያለው የሮማኖች ቍጥር አንድ መቶ ነበር።

24. የክብር ዘበኞቹ አዛዥ የካህናት አለቃ የነበረውን ሠራያን፣ ምክትሉንም ካህን ሶፎንያስንና ሦስቱን በር ጠባቂዎች አስሮ ወሰዳቸው፤

25. በከተማው ውስጥ ከቀሩትም ሕዝብ፣ የተዋጊዎቹ ኀላፊ የነበረውን መኰንን፣ ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች ከአገሬው ሕዝብ ወታደር የሚመለምለውን መኰንን ጸሓፊና በከተማው ውስጥ የተገኙትን ሌሎች ስድሳ ሰዎች ወሰደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 52